ሮሜሉ ሉካኩ ስላጋጠመው የጎል ድርቅ ምክኒያት ተናገረ

 

 7.jpg

በማንችስተር ዩናይትድ መልካም አጀማመር አድርጎ ነገርግን ከባለፈው መስከረም ወር በኋላ ለክለቡ ጎል ማስቆጠር የተሳነው ሮሜሉ ሉካኩ ጎል ማስቆጠር ለምን እንደከበደው ተናግሯል፡፡

ዩናይትዶች 75 ሚሊየን ፓውንድ አውጥተው ከቼልሲ መንጋጋ በመንጠቅ ማስፈረም የቻሉት ሮሜሉ ሉካኩ ከክለቡ ጋር አጀማመሩ ያማረ በማድረግ በፍጥነት የተላመደ መስሎ ነበር፡፡

ቤልጄማዊው ተጫዋች በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች በሙሉ ለዩናይትዶች ጎሎችን እያስቆጠረ ቡድኑም በፕሪምየርሊግም ይሁን በቻምፕየንስ ሊጉ ውጤታማ ጉዞ እንዲያደርግ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ነገርግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጎል ጋር የተጣላ ይመስል የጎል አቅጣጫው ጠፍቶት ታይቷል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ተጫዋቹ የቡድን ተጫዋች /Team Player/ አለመሆኑን በመግለጽ ጎል ለማሰቆጠር ቡድኑ ኳስ ተቆጣጥሮና ተጭኖ በማጥቃት ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ በማድረግ ለጎል የሚሆኑ ኳሶች እየተመቻቹ ሊሰጡት እንደሚገባ እምነቱ አላቸው፡፡

በርግጥም ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ፍፁም ጥሩ ካለመሆኑ የተነሳ አጥቅቶ መጫወት ባለመቻሉ የተጫዋቹ የሜዳ ላይ አገልግሎት ውስን ሆኖ ታይቷል፡፡

በተለይም ቡድኑ ከሊቨርፑል ጋር ካደረገው ጨዋታ ጀምሮ እንደ አጀማመሩ ወጥ አቋም ይዞ መጓዝ ባለመቻሉ ሮሜሉ ሉካኩን እንደጎዳው ይታሰባል፡፡

የቅርብ ጓደኛው የሆነው እና ጉዳት ላይ የሚገኘው ፖል ፖግባ በጉዳት ከቡድኑም መለየት የተሳኩ ኳሶች ወደ ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ ባለመቻላቸው ሌላው ተጫዋቹን የጎዳው ነገር እንደሆነ ይታመናል፡፡

ከቀናት በፊት ቤልጄም ከሜክሲኮ ጋር 3-3 በተለያየችበት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሉካኩ ሁለት ጎል በማስቆጠር ከወር በኋላ የጎል አይኑን መግለጥ ችሏል፡፡ይህ ደግሞ በሳምንቱ መጨረሻ ከክለቡ ጋር ሆኖ ኒውካስትልን ሲገጥሙ ጥሩ መነቃቃት እንደሚፈጥርለት ይጠበቃል፡፡

8.jpg

በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳቡን የሰጠው ሉካኩ  “በቅርቡ እንደ አጀማመራችን ጥሩ አቋም እያሳየን አንገኝም፡፡አጀማመራችን ኳስ ተቆጣጥረንና የጎል እድሎችን ፈጥረን ተጋጣሚያችንን በሰፋ ጎል እናሸንፍ ነበር፡፡ነገርግን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ጥሩ አለመጫወታችን ለኔ በጣም ከባድ አድርጎብኛል፡፡ያ ደግሞ በውድድር ውስጥ የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡አሁን ግን ከጉዳት የሚመለሱ ተጫዋቾች ስላሉ አመቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረን አቋም በተሻለ መጫወት እንችላለለን፡፡ብዙ ኳሶችን መፍጠር እና ማግባትም እንችላለን፡፡”

ከቤልጄም ብሔራዊ ቡድን ጋር ወደ ጎል መመለሱ እረፍት እንደሰጠው የተጠየቀው ሉካኩ “በርግጥ እረፍት አግኝቻለው ነገርግን ወደ ጎል አስቆጣሪነቴ እንደምመለስ አውቃለው፡፡እውነቱን ለመናገር ጥሩ ነገር ተሰምቶኛል፡፡የተወለድኩት ጎል ለማስቆጠር ነው፡፡በኔ ትውልድ ከኔ በላይ ጎል ያስቆጠረ ያለ አይመስለኝም፡፡እኔ ሳጥን ውስጥ ያለ ነብር ነኝ፡፡”ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡

ዩናይትዶች ከባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ በመሸነፋቸው ከመሪው ማን ሲቲ በስምንት ነጥብ ርቀው ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡በቀጣዮቹ ሁለት ቅዳሜዎች በፕሪምየርሊግ ኒውካስትል እና ብራይተንን ከገጠሙ በኋላ ወደ ኤምሬትስ በማቅናት አርሰናልን ይገጥማሉ ሲመለሱ ደግሞ ከከተማቸው ባላንጣ ማን ሲቲ ኦልድትራፎርድ ላይ ይፋለማሉ፡፡ወደ ጥሎ ማለፍ ለማለፍ ጫፍ ላይ በደረሱበት የቻምፕየንስ ሊግ ጨዋታ ለማድረግ ደግሞ የእሮብ ሳምንት ወደ ስዊዘርላንድ በማቅናት ከባዜል ጋር የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

Advertisements