“እየመጣሁ ነው ጓዶች” – ፓትሪስ ኤቭራ 

ዌስትሀም ፓትሪስ ኤቭራ በልምምድ ላይ ጂፕ የተሰኘውን ቅንጡ መኪና በገመድ አስሮ እየጎተተ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በመልቀቅ ከማርሴይ ቢሰናበትም ከምንግዜው በላይ ጠንክሮ እንደሚመጣ አስታውቋል።  

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ግራ መስመር ተከላካይ ባሳለፍነው ሳምንት ከኢሮፓ ሊግ ጨዋታ መጀመር በፊት ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ ትንኮሳ የፈፀመበትን አንድ ደጋፊ በመማታታቱ እስከ ሰኔ 2018 ድረስ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) እገዳ የተጣለበት ሲሆን ይጫወትበት የነበረው የፈረንሳዩ ክለብ ማርሴይም የውል ስምምነቱን እንዳቋረጠበት አይረሳም። 

ነገርግን ባሳለፍነው ሳምንት የተከሰተው አስከፊ ሁነት በመንፈሱ ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማያሳድርበት የ 36 አመቱ ኮከብ በዛሬው ዕለት በይፋዊ የኢንስታግራም ገፁ ወደልምምድ መመለሱን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ለተከታዮቹ በመልቀቅ ለማሳየት ሙከራ አድርጓል። 

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የቀድሞው ቀያይ ሴይጣን “ምን አይነት ቀን ነው! ጓዶች ታውቃላችሁ ሰኞ ነው። በጣም ደስተኛ ሰኞ። የተወሰነ ወቅት ላይ ክብድ የሚልህ ስሜት ይሰማሀል። ነገርግን ሁሌም ፈገግ ማለት መቀጠልና ይህን ጨዋታ መውደድ አለብህ።

“እየመጣሁ ነው። እየመጣሁ ነው ጓዶች። እየመጣሁ ነው። ይህን ጨዋታ እወደዋለሁ።” በማለት የተናገረ ሲሆን ከተንቀሳቃሽ ምስሉ በተጓዳኝም ፈረንሳዊው ኮከብ ተከታዮቹ ለሰጡት ድጋፍ ምስጋና ያቀረበበትን መልዕክት አስተላልፏል። 

ኤቭራ በመልዕክቱ “የመባረክ ስሜት ይሰማኛል። መልካም ሰኞ፣ ሰነፍ አትሁኑ። ከብዙ ሰዎች ድጋፍና ጥንካሬ እያገኛችሁ ለምን ትፈራላችሁ። እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። .. ልዩ ምስጋና።” ሲል ገልጿል።   

Advertisements