ተቃርኖ / ማይክል ኦውን ማንችስተር ዩናይትድን አስመልክቶ የሰጠው አስተያየት የሊቨርፑል ደጋፊዎችን ለሁለት ከፍሎ እያከራከረ ነው

የቀድሞው የሊቨርፑል አይረሴ ተጫዋች ማይክል ኦውን በአንድ ወቅት ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ከማምራቱ ጋር በተያያዘ ካሪም ቤንዜማን አስመልክቶ የሰጠው አስተያየት የመርሲሳይዱን ደጋፊዎች ለሁለት ከፍሎ እያከራከራቸው ይገኛል። 

በአሁኑ ሰአት የክለቡ አለም አቀፍ የእግር ኳስ አምባሳደር ሆኖ እያገለገለ ያለው የቀያዮቹ የቀድሞ አጥቂ በአንድ ወቅት ለዩናይትድ ለፈረመበት ክስተት የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ ለነበረው ሚና ምስጋና በማቅረብ በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ የተመሰቃቀለ ስሜትን ፈጥሯል። 

የቀድሞው የእንግሊዝ አጥቂ ከአመታት በፊት የወቅቱ ፈረንሳዊው የሎስብላንኮስ ተሰላፊ የሆነው ቤንዜማን አሌክስ ፈርጉሰን ሊያስፈርሙት ባለመቻላቸው ፊታቸውን ወደ ኦውን በመቀየር ከፖል ኢንስ በኋላ ለዩናይትድ የፈረመ የመጀመሪያው የቀያዮቹ ተጫዋች መሆን መቻሉ አይረሳም። 

ኦውን ጉዳዩን በማስመልከት ሲናገርም “ቤንዜማን አመሰግነዋለሁ። ምክንያቱም ከእሱ ውጪ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ፈፅሞ አላመራም ነበር። ፈርጉሰን እኔ ልፈርም የምችለው ቤንዜማን ማግኘት ካልቻለ እንደሆነ ነግሮኛል። የተፈጠረውም ያ ነው።” ሲል ተናግሯል። 

ከዚህ የኦውን ንግግር ጋር በተያያዘም የተወሰኑ የክለቡ ደጋፊዎች የቀድሞው የክለቡ አጥቂ ክለባቸውን መወከል የማይችል አጥቂ መሆኑን በመግለፅ እየተቹት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የቀዮቹ ደጋፊዎች እያዘኑለት እና ሁኔታው ቀለል ተደርጎ እንዲታይ እየተሟገቱለት ይገኛል።

በማይክል ኦውን ንግግር ዙሪያ የተወሰኑ የሊቨርፑል ደጋፊዎች የተቃራነ አስተያየት 

ራቨን ዊክሀውግ : ስሙ፣ ከሪያል ማድሪድ በኋላ ወደሊቨርፑል መመለስ ፈልጎ የነበረ ቢሆንም ክለቡ ፍላጎት አልነበረውም። ስለዚህ ሌላ የስራ ቦታ አገኘ። ለእኔ አሁንም የሊቨርፑል አይረሴ ነው። 

ክሪስ ትሬስ : ከሱ በተጨማሪ ጋሪ ኔቭልንም የክለቡ አምባሳደር አድርጉት  

ስትዋርት ፒርስ : አምባሳደርነቱን ንጠቁት። ለአምባሳደርነት ቦታው ከእሱ በላይ የተመቹ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋቾች አሉ። 

ፋቢዮ ፍራንሲስ : አስተያየቱ የእራሱ ነው። ነገርግን ተገቢው ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ‘እሱ አምባሳደር መሆን ይገባዋል ወይ?’ የሚለው ነው።

ኮሊን ሆል : ለምንድነው ይሄን አጭበርባሪ አምባሳደራችን ያደረግነው? 

አንድሪው ሀቺንግስ : ይሄ ክለቡ እራሱን ከኦውን የሚያገልበት ሰአት ነው።

Advertisements