አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ከአትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከስራ አስፈጻሚ እጩዎች ምርጫ ውጪ ሆኑ

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚነት የትግራይ ክልልን በመወከል ለውድድር የታጩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ እራሳቸውን ማግለላቸው በክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተቀባይነት ማግኘቱን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት አቶ ሕሸ ለማ በሰጡት መግለጫ፥ ራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉት የአቶ ተክለወይኒ አሰፋ ፌዴሬሽኑ ተቀብሎ ዛሬ ማፅደቁን አስታውቀዋል።

ክልሉን በመወከል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለስራ አስፈፃሚነት የሚወዳደር ምትክ ሰው በዚህ ሳምንት ይፋ እንደሚደረግ ገልፀዋል። የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የድርሻውን የሚወጣ፥ ስፖርቱ በሁሉም ክልሎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲነቃቃ ሙያዊ ብቃትና የአመራር ክህሎት ያለው ሰው ከክልሉ ለመወከል እየተሰራ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፥ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ፌዴሬሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በመገናኛ ብዙሃን ባስተላለፉት ያልተገባ ንግግርና በፈፀሙት ስህተት ይቅርታ በመጠየቅ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን ትናንት በይፋ መግለፃቸው ይታወቃል፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ

Advertisements