“ካልዋሹኝ በቀር ሜሲ የውል ማራዘሚያ ስምምነት ፈርሟል” – ጃቪየር ቴባስ 

ሊዮኔል ሜሲ በባርሴሎና አዲስ የውል ስምምነት መፈራረሙን ክለቡ እንደነገራቸው የላሊጋው ፕሬዝዳንት ጃቪየር ቴባስ ገልፀዋል። 

ከዚህ ቀደም የባርሴሎናው ስራ አስፈፃሚ ኦስካር ግራሁ የላሊጋው ክለብ ለአርጀንቲናዊው ኮከብ አዲስ የህይወት ዘመን ውል ማራዘሚያ እንደሚያቀርብለት መናገራቸው የሚታወስ ቢሆንም ሜሲ የወረቀት ጉዳዮችን መጨረሱና ውሉ ላይ ፊርማውን ማኖሩ እያወዛገበ ቆይቷል። 

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ከሜሲ የውል ማራዘም ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ክፍተት ምክንያት አንዳንድ የእግር ኳሱ አለም ጉምቱ ፀሀፊያን የሜሲ ቀጣይ መድረሻ የት ይሆን የሚሉ የካታላኑን ኮከብ የዝውውር ትኩረት ውስጥ የሚከቱ ዘገባዎችን ሲሰሩ ሰንብተዋል። 

በሌላ በኩል ግን ቴባስ ከሰአታት በፊት በሰጡት መግለጫ ባርሴሎና “ካልዋሻቸው በቀር” በካታላኑ ክለብና በሜሲ መሀከል የውል ማራዘሚያ ስምምነት መፈረሙን የሚገልፅና የስፔኑን ክለብ ደጋፊዎች እፎይታ ውስጥ የሚከት መግለጫን ሰጥተዋል። 

ቴባስ ስለጉዳዩ ሲያስረዱም “ሜሲ የሚራዘም ውል ነበረው። ውሎች ይፋዊ የሚሆኑት ሲፈረሙ እንጂ ተፈርመዋል ተብሎ ሲነገር አይደለም። ካልዋሹኝ በቀር ሜሲ ለባርሴሎና ፈርሟል።” በማለት የላሊጋው አስተዳዳሪ የበላይ አካል የሚያውቁትን ተናግረዋል።

ባሳለፍነው መስከረም የባርሴሎናው ፕሬዝዳንት ጆሴ ማሪያ ባርቶሚዮ ሜሲ በእሱ ስም አባቱ በፈረሙት የአምስት የውል ስምምነት ውስጥ ሆኖ እየተጫወተ እንደሆነ መናገራቸው የሚታወስ ቢሆንም በስምምነቱ ዙሪያ ይፋዊ ማረጋገጫ ከላሊጋው ክለብ አለመሰጠቱ በደጋፊዎች ዘንድ ስጋትን የፈጠረ ክስተት ሆኖ ቆይቷል።

ባርቶሚዮ ባሳለፍነው ወር ጥቅምት በስካይ ቴሌቭዥን በነበራቸው ቃለመጠይቅም “ሜሱ በአዲሱ ስምምነት መሰረት ክፍያ እያገኘ ነው። የቀረው ነገር ከፕሬዝዳንቱ ጋር ፎቶ አለመነሳቱ ብቻ ነው።” በማለት የአርጀንቲናዊውን ውል መራዘም መግለፃቸው አይረሳም።  

በሌላ በኩል የ 30 አመቱ የአምስት ጊዜያት የባለንዶር አሸናፊው ሜሲ ባሳለፍነው ሳምንት ከአንድ የሀገሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበረው ቆይታ ወደልጅነት ክለቡ ኒውዌልስ ኦልድ ቦይስ ዳግም የመመለስ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል። 

ሜሲ “ፍላጎቴ ሁሌም ለኒውዌልስ መጫወት ነው። እሱ በልጅነቴ ሳልመው የነበረው ነው። ወደክለቡ ሳመራ በፕሪምየራ ዲቪዚዮን መጫወትን አልማለሁ። ነገርግን በጥቂት አመታት ውስጥ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም።

“ወደዛ አልመለስም ብዬ መናገር አልችልም። ወዴት እንደማመራ አላውቅም።” በማለት ቀጣይ ቆይታው ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ መሆኑን አስታውቋል።  

​ሜሲ ከቀናት በፊት አፈትልኮ የወጣ በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጨ ምስል ከወራት በኋላ በሚደረገው የ 2017 የፍራንስ ፉትቦል መፅሄት የአለም ኮከብነትን ክብር እንዳገኘ ከወዲሁ እየተነገረለት ይገኛል።

ሜሲ የ 2017 የፍራንስ ፉትቦል የአመቱ ኮከብ ተጫዋች መሆኑን የሚያሳየው አፈትልኮ የወጣ ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያ ሲናፈፅ የነበረው የመፅሄት ሽፋን ምስል ይህን ይመስላል።

ይህን ከሽልማት አዘጋጁ ፍራንስ ፉትቦል መፅሄት ይፋዊ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ያልተሰጠበትን ምስል እውነተኛነት ከተቀበሉ አንዳንዶች እየተነሳ ያለው መከራከሪያ ከአመት በፊት በ 2016 በነበረው ምርጫ የሮናልዶ የሚያሳይ ምስል ከስነስርዓቱ ቀደም አፈትልኮ መውጣቱና አሸናፊው ፖርቹጋላዊው ተጫዋች ሆኖ መገኘቱ ነበር። 
 

Advertisements