ዳንኤል ዴ ሮሲ ተቀይሮ እንዲገባ ሰውነቱን እንዲያፍታታ ሲጠየቅ ለምን ፍቃደኛ ሳይሆን ቀረ?

De-Rossi-told-Italy-boss-not-to-bring-him-on.jpg

ጣሊያን ከ 60 አመት በኋላ ከአለም ዋንጫው ተሳትፎ ውጪ መሆኗን ባረጋገጠችበት የትናንት ምሽቱ ጨዋታ ላይ የቡድኑ አሰልጣኝ ጂያምፒሮ ቬንቹራ የሮማውን አማካኝ ዳኒኤል ዲሮሲን ቀይረው ወደ ሜዳ ለማስገባት ተጨዋቹ ሰውነቱን እንዲያፍታታ በረዳታቸው በኩል ጥያቄ ቢያቀርቡም ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

በሳን ሴሮ ከ72 ሺ በላይ የጣሊያን ደጋፊ ቡድናቸውን ለማበረታታት ቢገኙም ሜዳውን የለቀቁት ግን በከፍተኛ የሆነ የሀዘን ድባብ ነበር፡፡በተደጋጋሚ ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ታላቅነታቸውን ባረጋገጡበት መድረክ ከተሳትፎ ውጪ ሲሆኑ ተጫዋቾችን ጭምር ያስለቀሰ ሆኗል፡፡

ጣሊያኖቹ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ፍልሚያ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ቢያደርጉም በአጨራረስ ላይ የታየባቸው ችግር በመጀመሪያው ዙር ላይ ከገጠማቸው የ 1 ለ 0 ሽንፈት መቀልበስ ተስኗቸው ቡድናቸው ከ 1958 በኋላ ከአለም ዋንጫው ተሳትፎ ውጪ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል፡፡

ለሽንፈቱም የቡድኑ አሰልጣኝ ጂያምፒሮ ቬንቹራ የመጀመሪያ ተጠያቂ በማድረግ ጠንካራ ትችቶች እየቀረበባቸው ቢገኝም እሳቸው ግን ከጨዋታው በኋላ በውጤቱ “ይቅርታ” ሲሉ ሀላፊነቱን ወስደዋል፡፡ከሀላፊነታቸውም ከእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር ከተወያዩ በኋላ እንደሚነሱ ይጠበቃል፡፡

በጨዋታው ጎል የግድ ያስፈልጋቸው የነበሩት አዙሪዎቹ ያላቸው የመጨረሻ አቅም በመጠቀም የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ወደ ሜዳ ሊያስገቡ አለመቻላቸው አስገራሚ ሆኗል፡፡በተለይም በናፖሊ መልካም ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ሎሬንዞ ኢንሲኝ ወደ ሜዳ እንዲገባ ደጋፊዎች ጫና ቢያሳድሩም አሰልጣኙ ግን ወደ ሜዳ ለመቀየር ሰውነቱን እንዲያፍታታ በረዳታቸው አማካኝነት ያዘዙት የሮማው አማካኝ ዳንኤል ዴ ሮስን ነበር፡፡

ተጫዋቹ ግን ከአሰልጣኙ የመጣውን ጥያቄ በቁጣ መልሶታል፡፡“ለምንድነው እኔ የማማሙቀው? እኛ አቻ መውጣት አንፈልግም ማሸነፍ እንፈልጋለን፡፡”በማለት በምልክት ወደ ሎሬንዞ ኢንሲኝ በመጠቆም  ተቀይሮ መግባት  የሚገባው ኢንሲኝ ነው በማለት በቁጣ ነግሯቸዋል፡፡

63.jpg

ነገርግን ኢንሲኝ ወደ ሜዳ ተቀይሮ ሳይገባ ጨዋታው በጣሊያን ሽንፈት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ጂያምፒሮ ቬንቹራም በቆይታቸው የወቅቱ ምርጥ የሴሪ ኣ ተጫዋችን ለምን ለመጠቀም እንዳመነቱ ባለመታወቁ ለጠንካራ ትችት ተዳርገዋል፡፡

ዴ ሮሲ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከራይ ቴሌቭዥን ጋር ያደረገው ቆይታ የአሰልጣኙን ውሳኔ መቃወሙን ያመነ ቢሆንም ላደረገው ነገርም ይቅርታ ጠይቋል፡፡የጨዋታው መጠናቀቅ እየደረሰ በመሆኑ ማሸነፍ እንደሚገባን በመጥቀሰ ሰውነቱን ማፍታታ የሚገባው የአጥቂ ተጫዋች በመሆኑ ወደ ኢንሲኝ ጠቁሚያለው በማለት ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡

ዳንኤል ዲ ሮሲ እንደ ጂጂ ቡፎን ሁሉ ከጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ጫማውን የሰቀለ በመሆኑ ከአሁን በኋላ ለሀገሩ ተሰልፎ አይጫወትም፡፡አንጋፋዎቹ ሁለቱ ተጫዋቾች ጣሊያን በ 2006 የአለም ዋንጫ ስታሸንፍ የቡድኑ አካል እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

 

63.jpg

Advertisements