ድህረ ማጣሪያ / የከሸፈ ራዕይ፣ ሀዘን፣ ቁጭት፣ ውድቀት … ሀገረ ጣሊያን በፅልመት ውስጥ ምን ትመስል ይሆን? 

“ይህ ለመላው የጣሊያን እግር ኳስ ሀዘን ነው።” የሚለው ተስፋ አስቆራጭና ልብ ሰባሪ ንግግር ከዲኖ ዞፍ በኋላ ጣሊያን በታሪኳ የተመለከተችው ድንቁ ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎን ሀገሩ ከ 60 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ከአለም ዋንጫው ስትቀር እንባ እየተናነቀው ስንብቱን ያስታወቀበት መንገድ ነው። ይህ የአሮጊቶቹ ግብ ጠባቂ ንግግር ግን የመላውን ጣሊያን የወቅቱን ሀዘን በጥቂቱ ቢገልፅ እንጂ ትክክለኛው ማሳያ እንዳልሆነ የኢትዮአዲስ ስፖርቱ ሚኪያስ በቀለ በቀጣይ ፅሁፉ ሊያሳየን ከጣሊያን ጋዜጦች እስከ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ድረስ ያለውን ድባብ እንደሚከተለው ይዞ ተገኝቷል።     


የአራት ጊዜዋ የአለም ዋንጫ አሸናፊ ጣሊያን ወትሮም ስትጠበቅ መንሸራተት ሳትጠበቅ ደግሞ ብዙዎችን ድባቅ መታ ድል ማድረግ የሰርክ ተግቧሯ ነው። ትናንት ምሽት የሆነውም ያ ነበር። 

በምሽቱ ፍልሚያ ጣሊያን በስዊድን ተረታ ከአለም ዋንጫው ውጪ ከሆነች በኋላ ለሀገሩ 175 ጨዋታዎችን ያደረገው የ 39 አመቱ ቡፎን “እዝናለሁ! ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለመላው የጣሊያን እግር ኳስ ይህ የሀዘን ወቅት ነው።” 

“በማህበራዊ ደረጃ ጭምር ትልቅ የሆነ ነገር ያጣነው። ይህ ለእኔ ብቸኛው አሳዛኝ አጋጣሚ ነው። የመጨረሻው ጨዋታዬ ከእንደዚህ አይነቱ አጋጣሚ ጋር በመግጠሙ በጣም አዝናለሁ።”  ከማለት ውጪ ተጨማሪ ቃላት ማውጣት አልተቻለው።

ይህ ከ 1958 በኋላ በተከሰተው ‘የውጤት ግርዶሽ’ ምክንያት የመጣው የግራዚያኒዋ ሀገር ዋይታና ለቅሶ ግን በጣሊያን ጋዜጦች በትልቁ ሲስተጋባ የዋለ እና የአዙሪዎቹን ህመም በተሻለ መልኩ ያሳየ ነበር። 

ከሀገሪቱ ትልቁ ተነባቢ ጋዜጣ ላ ጋዜጣ ዴሎ ስፖርት ብንጀምር በፊት ገፁ “ከታይታኒክ ጋር የሚመጣጠን ስፖርታዊ ክስተት ነው” ከሚል መግቢያ ፅሁፍ ጋር “ፍፃሜው” የሚል ትልቅ ርዕስ ይዞ ወጥቷል።  

በነፃ አሳቢነቱ (Liberal) የሚታወቀው ላ ሪፐብሊክ የተሰኘው የጣሊያን ጋዜጣ በበኩሉ ከምስል ጋር “የደበዘዘ የአዙሮው ራዕይ” የሚል ርዕስ በፊት ገፁ ሲያወጣ ላ ስታምፕ በበኩሉ “የአዙራ ራዕይ” ሲል በፊት ገፁ በትልቁ በለቀቀው ፅሁፍ በሀዘን ውስጥ በንዴት መንፈስ ተሳልቋል።

ይህ የትናንት ምሽቱ ውጤትም የቡፎንን የብሔራዊ ቡድን ቆይታ ብቻ ሳይሆን የቋጨው ሌሎቹን የቡድኑን የረጅም ጊዜ ተሰላፊዎች የሆኑትን ዳንኤል ደ ሮሲ፣ አንድሬ ባርዛግሊ እና ሊኦናርዶ ቦኑቺን ስንብትም ያስከተለ አሳዛኝ ፍፃሜ ነበር።  

ደሮሲ የምሽቱን ክስተት ይዞት የመጣውን አደጋ የገለፀውም “ይህ ወቅት ለእኛ እግር ኳስ የፅልመት ወቅት ነው። ለሁለት አስርታት የዚህ ቡድን አካል ለነበርነው ለእኛ በጣም የደበዘዘ ጊዜ ነው።” በማለት ነበር።

በዚህ ሁሉ መሀከል ግን ቡፎን በእንባ ታጅቦም ጣሊያን በእግር ኳስ ወድቃ እንደማትቀር የሀገሩ እግር ኳስ በአዲሱ ትውልድ እንደሚያንሰራራ በመግለፅ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ፍንጣቂ ብርሀንን እንካችሁ ለማለት ሙከራ አድርጓል።  

በዘንድሮው ከ 21 አመት በታች በአውሮፓ ሻምፒዮና ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰውና ከ 20 በታች የአለም ዋንጫን ሶስተኛ ደረጃን ያገኘው የጣሊያን አዲሱ ትውልድም ቡፎን ያቀበለውን አደራ ተከትሎ በቀጣዩ ጊዜ የአዙሪዎቹን እግር ኳስ ዳግም ከዝና ማማ ካልሰቀለ የታላላቆቹን አደራ እንደበላ ይቆጠራል። 

ከላይ ላለው አባባል ማስረጃችን ደግሞ በቡፎን ገለፃ ጣሊያን የኩሩዎች፣ የችኮዎች፣ የጠንካራ ሰራተኞች እና ሁሌም በመጥፎ ውድቀት ውስጥ እራሳቸውን ከፍ ማድረግ የሚችሉ ዜጎች ያሉባት ሀገር መሆኗ ነው። 

Advertisements