ጣሊያን ከ 60 አመት በኋላ ከአለም ዋንጫ ተሳትፎ ውጪ ሆነች

በምሸቱ ጨዋታ ላይ የፈጠሩት የኳስ የቁጥጥር የበላይነት ውጤት ያልገዛላቸው ጣሊያኖቹ በስዊድን በአጠቃላይ ውጤት 1 ለ 0 ተሸንፈው ለአራት ጊዜ ከተሞሸሩበት የውድድሮች ሁሉ ቁንጮ ከሆነው የአለም ዋንጫ ተሳትፎ ውጪ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

72ሺ ደጋፊ በግዙፉ ሳንሲሮ ስታድየም አንገት የደፋበት፣የቀድሞ ባለ ግርማ ሞገሱ ሰማያዊ በነጭ ቁምጣ የሆነው የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን መለያ አድርገው የገቡት ተጫዋቾች ስዊድንን መርታት ተስኗቸው አይናቸው በእንባ አጅበው በቁጭት ሜዳ ላይ ተዘርረው የታዩበት፣ለስካንዴኒቪያ አገሯ ስዊድን ጡዘት፣ፌሽታ፣ወደር ያልተገኘለት ስሜት የአራት ጊዜ የአለም ዋንጫ አሸናፊዎቹ አዙሪዎቹን ከ 2018 የአለም ዋንጫ ተሳትፎ ውጪ ማድረጉ ሲረጋገጥ የተፈጠረ የሁለት ቡድኖች የተቃራኒ ስሜት ነበር።

ሚላን ላይ የከተሙ የአዙሪዎቹ ደጋፊዎች ከጨዋታው በፊት ከ2006 በኋላ ወደ አለም ዋንጫ ያልተመለሰችውን ስዊድን አሸንፈው ታላቅ ክብር ወዳገኙበት የውድድሮች ሁሉ ቁንጮ ወደሆነው የአለም ዋንጫ ላይ እንደሚቀርቡ የእርግጠኝነት ስሜት ፊታቸው ላይ ይነበባል።

አርብ ለታ በስቶኮልም የመጀመሪያው ጨዋታ ጃኮብ ጆንሰን መትቶ ተጨርፋ የተቆጠረችው ጎል ምክንያት የ 1 ለ 0 ሽንፈት ቢገጥማቸውም በሜዳቸው ሊያውም በግዙፉ ሳንሲሮ የሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ ስዊድን ረትተው አይናቸውን ከዋክብቶች መናኸሪያ ወደሚሆነው ታላቁ ውድድር እንደሚሳተፉ አምነው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙዎቹ ጣሊያኖቹ ከጨዋታው የሚፈለገውን ውጤት ካላገኙ ለሀገሪቷ እግርኳስ ልሽቀት እንዲሁም በአለም ዋንጫው አለመሳተፋቸው ደግሞ የውድድሩን ውበት የማደብዘዝ አቅም እንዳለው በስፋት ሲናገሩ ቆይተዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጣሊያን ተጫዋቾች ስሜት

 ደቂቃዎች ሲነጉዱ ውጥረቶች እየጨመሩ በሄዱበት የምሽቱ ጨዋታ ጣሊያኖቹ ለጎል የቀረቡ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም የስዊዲናዊው ግብ ጠባቂ ኦልሰን መረብ ለመንካት ተቸግረው ታይተዋል።

አጨራረስ ላይ የነበራቸው ድክመት እና በመጨረሻ የአደጋ ክልል ላይ የነበራቸው ያልተሳኩ ቅብብሎች በጨዋታው ዋጋ ከፍለው ጎል እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል።

ይህ ደግሞ በአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ አራት ተጫዋቾችን ብቻ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድኗ አካታ በመጀመሪያ ጨዋታ ላይ 1 ለ 0 ስቶኮልም ላይ ማሸነፍ ለቻለችው ስዊዲን ወደ ራሺያው የአለም ዋንጫ ለማቅናት በቂዋ ሆኖላታል።

በምድብ ድልድሉ በሶስተኛ ቋት(Pot) ላይ የነበሩት ስዊድኖቹ ኔዘርላንድ እና ፈረንሳይ በሚገኙበት ጠንካራ ምድብ የምድቡ አባት የነበረችውን ኔዘርላንድን ቀድማ ከምድቧ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቋ ለጣሊያንም ቀላል ተፎካካሪ እንደማትሆን ቅድሚያ ስጋታቸውን ላስቀመጡ ሰምሮላቸዋል።

ለጣሊያኖቹ ውድቀት እንደ አንድ ምክንያት የቀረበው ደግሞ ከጅምሩ በምድብ ድልድሉ በ ሁለተኛ ቋት(pot) ላይ መገኘታቸው እንደ ስፔን አይነቷን ታላቅ አገር ጋር በአንድ ምድብ ለመፋለም መገደዳቸው ወደ አለም ዋንጫው በቀጥታ እንዳያልፉ ሳንካ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ አድርገውታል።

ሽንፈቱ አዙሪዎቹን ከ 1958 በኋላ በታላቁ መድረክ ላይ እንዳይሳተፉ ሲያደርጋቸው ስዊድንን ደግሞ ከ 2006 በኋላ ወደ አለም ዋንጫ እንዲመለሱ አድርጓቸዋል።ስዊድን ለመጨረሻ ጊዜ ተሳትፎ ባደረገችበት የ 2006 የአለም ዋንጫ ላይ አሸናፊ የሆነችው ጣሊያን እንደነበረች ይታወሳል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጣሊያን ተጫዋቾች በጉልበታቸው በመንበርከክ እና በደረታቸው በመተኛት እንባቸውን በማውረድ በከፍተኛ ቁጭት ውስጥ ሆነው ታይተዋል።

ለአንጋፋው ግብ ጠባቂ የ 39 አመቱ ጂጂ ቡፎን ደግሞ የሀገሩን ማሊያ ለመጨረሻ ጊዜ ለብሶ በአለም ዋንጫ ላይ ከተሳተፈ በኋላ ጫማውን እንዳይሰቅል ከወዲሁ ሩጫው እንዲያበቃ በመደረጉ ሀዘኑን ከጨዋታው በኋላ በእንባ ገልጿል።”የመጨረሻዬ ጨዋታ ላይ በሽንፈት ከአለም ዋንጫ ተሳትፎ ውጪ በመሆናችን በጣም ያበሳጫል።”ሲል ተናግሯል።

አሰልጣኙ ጂያን ፒሮ ቬንቹራም ከሀላፊነታቸው እንደሚለቁ የሚጠበቅ ሲሆን በቅድሚያ ግን ከፌዴሬሽኑ ጋር መወያየትን መርጠዋል።”በውጤቱ ይቅርታ እጠይቃለው።” ሲሉም ከጨዋታው በኋላ ተናግረዋል።

ዴ ሮሲ ከብሔራዊ ቡድኑ ጫማውን የሰቀለ ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል

በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው የሮማው ዴ ሮሲን እንደ ቡፎን ሁሉ መልሶ ለሀገሩ እንደማይጫወት አሳውቋል።ተከላካዮቹ ቼሊኒ እና ቤንዛግሪም የሱን ሂደት ተከትለው ከብሔራዊ ቡድኑ ጡረታ እንደሚወጡ ይጠበቃል።

Advertisements