አዙሪት / ሀገረ ጣሊያን የአለም ዋንጫ ምስቅልቅል ይዞባት የመጣው ኪሳራ ከተጠበቀው በላይ መዘዝ እንደሚኖረው የማይካድ ሀቅ ሆኗል  

ሀገረ ጣሊያን ላለፉት 60 አመታት ብዙ መከራዎችን አስተናግዳለች። ባለፉት ስድስት አስርታት እልፍ መሪዎቿ ከስልጣን ማማ ላይ ወድቀው ሲቀሩ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደሞ የመሬት መንቀጥቀጥና የማፊያ ሽብር ሲንጣት ተስተውሏል። ነገርግን እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ከ 1958 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡድኗ ለአለም ዋንጫ ሳያልፍ የቀረበትን እና በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች ጭምር ተጠያቂ የተደረጉበትን የሰኞውን ክስተት አንደማይወዳደሩ የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለ ሊያሳየን ልዕለ አውሮፓዋ ሀገር ከእግር ኳሷ ጋር በተያያዘ የተቃጣባትን ከባድ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያነሳ እንደሚከተለው ይሞግተናል። 


በጎዶሎው ሰኞ ምሽት ጢም ባለው የሳንሲየሮ ስታዲየም የሆነው በሙሉ ለባህል ተኮር ተንታኞች የጣሊያን ማህበረሰብ ወደ ዘመናዊነት የሚያደርገው ጉዞ ውድቀት መገለጫ ነው። 

እንደ እነሱ አባባል በጣሊያን እግር ኳስ ፌደሬሽን ውስጥ የተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አሰራር የውድቀቱ መነሻ ነው። የእምዬን ወደ አብዬ በሚያስብል መልኩ አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ ለክስተቱ ድህነትን ለማሸነፍና ጦርነትን ሽሽት በስደት ሀገራቸው የመጡ ስደተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እጃቸውን ወደነሱ ለመቀሰር ሲሯሯጡ ታይተዋል።  

ይህ በ 60 አመት አንዴ የደረሰ የጣሊያን ውድቀት ካስከተለው የባህልና ማህበራዊ ስንክሳር በተጨማሪ ሀገሪቱ ላይ የ 1 ቢሊዮን ዩሮ (1.5 ቢሊዮን ዶላር) ኪሳራ የሚያስከትል ዘርፈ ብዙ ችግር ነው።  

የቀድሞው የሀገሪቱ እግር ኳስ ፕሬዝደንት ፍራንኮ ካራሮ ጉዳዩን ሲያስረዱም “ይህ የማስታወቂያ፣ የቴሌቪዥን መብት እና ከአለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ በውድድሩ ላይ የሚገኝ ገቢ የማጣት ጉዳይ ብቻ አይደለም። 

“ከዛ በላይ የከፋና በውድድሩ ላይ በመላው ሀገሪቱ ባሉ መጠጥ ቤቶች ለቁማርና መሰል ወጪዎች የሚወጣውን የመዝናኛ ገንዘብ ዝውውር ትተነው ለአለም ዋንጫው የጉዞ ወኪሎች በልዩ ሁኔታ የሚያዘጋጁትን የመጓጓዣ አቅርቦት ገቢ የሚያሳጣ ጭምር ነው።” ብለዋል።

ከጣሊያን የአለም ዋንጫ ውጪ መሆን ጋር በተያያዘም ዕለታዊውን ንግድ ተኮር ጋዜጣ ሶል 24 ኦርን ጨምሮ ብዙ የዋጋ ተንታኞች በመጪው ጊዜያት ከሀገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ቀጥታ ስርጭት ጋር በተያያዘ የሚኖረውን የገቢ ማሽቆልቆል ትኩረት ሰጥተው ዘገባ እየሰሩበት ሲሆን በመነሻነትም 100 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራን እንደሚያስከትል ገልፀዋል።

ካራሮ እንደሚሉት ከሆነም ለአራት ጊዜዋ የአለም ዋንጫ አሸናፊ ከታላቁ ውድድር ተሳትፎ ውጪ መሆን ከረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ መዳከም በብርቱ ሁኔታ እያንሰራራ ለነበረው የጣሊያን ኢኮኖሚ በመጪው ጊዜ ረጅምና ሰፊ ተፅዕኖ የሚያመጣ የዳግም ቁልቁለት ሂደት አካል ነው።

“ቡድናችን ለአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ከክረምት 2018 በኋላ ጨዋታ ማድረግ ከመጀመሩ በፊት ይፋዊ ጨዋታዎች ማድረግ አይጀምርም። ይህም ማለት ሌሎች የወዳጅነት ጨዋታዎች የስፖንሰርና የቴሌቪዥን መብቶችን ጨምሮ አነስተኛ ፍላጎትና ገቢን የሚስቡ ናቸው።” በማለትም ካራካስ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

የጣሊያን ያልተሳካ ጉዞ ግን በዚህ የማይቋጭና በማሊያ ሽያጭ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው ነው። ለዚህ ማሳያው የሀገሪቱ ብሔራዊ ቡድን መለያ አቅራቢ የሆነው የጀርመኑ ትጥቅ አምራች ድርጅት ፑማ ጣሊያን ለአለም ዋንጫው አለማለፏ ከታወቀ በኋላ የድርሻ ገበያው ማሽቆልቆሉ ዋነኛው ማሳያ ነው።

የትጥቅ ተንታኝ የሆኑት ቺን ግራዙቲስ ከብሉምበርግ ጋር በነበራቸው ቆይታም ጣሊያን ለአለም ዋንጫ ካለማለፏ ጋር በተያያዘ በነጠላ ፑማን 1.5 ሚሊዮን ማሊያዎች ሽያጭ እንደምታሳጣው የገለፁ ሲሆን በአማካኝ አንዱ ከ 80 እስከ 90 ዶላር ዋጋ ሲተመንም ፑማ የ 140 ሚሊዮን ዶላር የችርቻሮ ትርፍን እንደሚያጣ አስልተውለታል።

በአጠቃላይ ሲታይ ፑማ የጣሊያን ከአለም ዋንጫው መቅረት በሽያጭ ገቢዬ ላይ ለውጥ አያመጣም እያለ የአልከሰርኩም መግለጫን ቢያወጣም አውሮፓዊቷ ሀገር እና የጀርመኑ ትጥቅ አምራች ድርጅት ካሳለፍነው ሰኞ ምሽት አንስቶ የእንዘጭ እምቦጭ ጉዟቸውን ከወዲሁ ተያይዘውታል።   

Advertisements