ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለምን ሊዮ ሜሲ ጋር በሚስጢር ስልክ ደወለ?


በ ዕዮብ ዳዲ


ሁለቱ የአለማችን ኮከብ ተጫዋቾች የሆኑት ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮ ሜሲ ባልተለመደ ሁኔታ በሚስጢር በስልክ ተገናኝተው አውርተዋል።የስልክ ቁጥሩን የመታው ደግሞ ፓርቹጋላዊው ኮከብ እንደሆነ ተሰምቷል።

አለማችን ካፈራቻቸው ድንቅ ተጫዋቾች ውስጥ የሚካተቱት ሊዮ ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ባለፉት አስር አመታት የአለም ኮከብ ተጫዋቾች እየተባሉ እየተፈራረቁ ማሸነፍ ችለዋል።

ደጋፊዎቻቸው ጎራ ፈጥረው የሁለቱ ተጫዋቾች የግል እና የቡድን ሪከርዶችን እየመዘዙ ላለፉት ረጅም አመታት ሲሟገቱም ቆይተዋል።

የሊዮ ሜሲ አድናቂዎች በተጫዋቹ የቴክኒክ ብቃት በመማረክ ለኳስ የተፈጠረ ሲሉ ያወድሱታል።ሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ያለውን ስነምግባርም ለወጣት ተጫዋቾች ትክክለኛ አርአያ መሆን የሚችል ተጫዋች መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ሮናልዶን የሚሉ ደግሞ በጠንካራ ስራ እራሱን ለኮከብነት ያበቃ፣ታታሪነቱን በማሞካሸት በተጫዋቹ የሜዳ ላይ ትጋት በማሞገስ ቁጥር አንድ መሆኑን ይመሰክራሉ።

የሁለቱ ኮከቦች ባላንጣነት 2017 ላይም በመቀጠል በተለያዩ የግል እና የቡድን ክብሮች አሳልፈዋል።በተለይም ሮናልዶ ከሪያል ማድሪድ ጋር የላሊጋን ክብር እንዲሁም የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል።

በቀጣይ ወርም ይፋ የሚደረገው የባሎንዶር ሽልማት ከሁለቱ ኮከቦች እንደማያልፍ የሚጠበቅ ሲሆን ክርስትያኖ ሮናልዶ የማሸነፍ ሰፊ እድል እንዳለው እየተነገረ ይገኛል።

ነገርግን ከሰሞኑ አፈትልከው የወጡ አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ ሊዮ ሜሲ ለስድስተኛ ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊ እንደሚሆን የሚገልፁ ሆነዋል።

እንደ ስፔኑ ዶን ባሎን ዘገባ ሜሲ እና ሮናልዶ በሚስጢር በስልክ ስለ 2017 የባሎንዶር አሸናፊ ጉዳይ ተወያይተዋል።ስልኩን የደወለው ሮናልዶ ሲሆን ለአምስተኛ ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊ መሆኑን ለመንገር ለሜሲ ደውሎ ነግሮታል።

ሜሲም “እንኳን ደስ አለህ”ሲል ለማድሪዱ ኮከብ ምላሽ ሰጥቶታል።ነገርግን ሮናልዶ በ 2017/2018 የውድድር አመት አቋሙ በመውረዱ ከወዲሁ ሊዮ ሜሲ የ 2018 ባሎንዶር እንደሚያሸንፍ እምነት እንዳደረበት ዶን ባሎን ጨምሮ ገልጿል።

ሜሲ ዘንድሮ በላሊጋው 12 ጎሎችን በማስቆጠር በግሉም ይሁን ከቡድኑ ጋር አስደናቂ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን ሮናልዶ በተቃራኒው አንድ ጎል ብቻ በማስቆጠር ከማድሪድ ጋር ደካማ አቋም እያሳየ ይገኛል።

ብራዚላዊው ካካ ደግሞ የሁለቱ ኮከቦች ተከታታይ የባሎንዶር አሸናፊነት የሚሰብረው ኔይማር እንደሆነ ገልጿል።”እግርኳስ ትክክለኛ የሆነ ሳይንስ አይደለም።ስለዚህ ወደፊት ምን እንደሚከሰት ማወቅ አይቻልም።ነገርግን ከሮናልዶ እና ሜሱ በመቀጠል ኔይማር አሸናፊ ይሆናል።”ሲል ተናግሯል።

ውድ የድረ ገጻችን ተከታታዮች ከወር በኋላ ይፋ የሚደረገው የ 2017 የባሎንዶር አሸናፊ ማን ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ?ከማድሪድ ጋር ውጤታማ አመት ያሳለፈው ሮናልዶ በሊዮ ሜሴ የመቀደም እድል ይኖረው ይሆን? ሀሳባችሁን በኮሜንት ሳጥን ውስጥ አስቀምጡ።

Advertisements