“ዘረኝነት” ከእግርኳስ ሜዳዎች ሊጠፋ ያልቻለ ማነቆ

ኮሎምቢያዊው ኤድዊን ካርዶና በደቡብ ኮሪያ ተጫዋቾች ላይ ያሳየው የዘረኝነት ምልክት ሀገሩን ያሳፈረ ደቡብ ኮሪያን ደግሞ ያስቆጣ ሆኖ መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል።

እግርኳስ የተለያዩ ሀገራትን፣ማህበረሰቦችን ቋንቋን፣ዘር፣ሀይማኖትን እና እድሜን ሳይለይ ሁሉንም በአንድ መንፈስ አንድ ማድረግ የሚችል ትልቅ መድረክ መሆኑ ግልፅ ነው።

ነገርግን አልፎ አልፎ ተጫዋቾች እንዲሁም ደጋፊዎች የቆዳ ቀለምን እና ተፈጥሯዊ አካላዊ ቅርጾች ምክንያት በማድረግ የሚያሳዩት ያልተገባ የዘረኝነት ስድቦች ወዳልተገቡ ረብሻዎች ሲያመሩ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

በዘረኝነት ስድቦች ምክንያት ተጫዋቾች ጨዋታ አቋርጠው ሲወጡ፣አፀያፊ ስድቦች ለደጋፊዎች ሲመልሱ እንዲሁም ከእግርኳስ ተመልካቹ አልፎ ሀገራትን ሊያቀያይም የሚችል የእግርኳስ ማነቆ ነው።

በስፓርታዊ መድረኮች ላይ የሚታዩ የዘረኝነት ስድቦች ላለፉት ረጅም አመታት በተለያየ መልኩ የነበሩ ሲሆን በሚያሳዝን ሁኔታ አሁንም የቀድሞው ያህል ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ቀጥለው የሚድያ ትኩረት ሆነዋል።

ባለፈው አርብ ሴኦል ላይ ኮሎምቢያ ከ ደቡብ ኮሪያ ጋር ያደረገችው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በስፐርሱ ሶን ሁንግ ሚን ሁለት ጎሎች ደቡብ ኮሪያ 2-1 ማሸነፍ ብትችልም የ24 አመቱ ኮሎምቢያዊው ተጫዋች ኤድዊን ካርዶና ያሳየው የዘረኝነት ስድብ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።

የአካል ንክኪ በበዛበት ጨዋታ በሁለተኛው ግማሽ ላይ በአንድ አጋጣሚ በሁለቱ አገሮች ተጫዋቾች መካከል የተፈጠረው ግርግር ለአርጀንቲናው ቦካ ጁኒየርስ በውሰት እየተጫወተ የሚገኘው ካርዶና አይኑን ወደ ጎን በመበልጠጥ በደቡብ ኮሪያ ተጫዋቾች ላይ ሲሳለቅ በቴሌቭዥን ካሜራ እይታ ውስጥ ወድቋል።

ኤድዊን ካርዶና የኮሪያ ተጫዋቾች ላይ የተሳለቀበት መንገድ

ኮሪያዎች በተፈጥሯቸው አይናቸው ጠበብ እና አነስ ያለ በመሆኑ ኮሎምቢያዊው ተጫዋች የአይናቸውን ትንሽነት በምልክት በመግለፅ የዘረኝነት ስድብ በመስደቡ መላው የኮሪያ ህዝብን ያስቆጣ ድርጊት ሆኗል።በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም የሰላ ትችት ቀርቦበታል።

የቡድኑ አሰልጣኝ ሆዜ ፔኬርማን የተጫዋቹ ድርጊትን አስመልክቶ ከጨዋታው በኋላ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በምልክት የተሳደበውን አልተመለከትኩም ስለዚህ አስተያየት ለመስጠት አልችልም።ጨዋታው የአካላዊ ንክኪ የበዛበት ነበር፣በእንደዚህ አይነት ጨዋታ ደግሞ የተለዩ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ከዚህ በላይ በአይኔ ላልተመለከትኩት ነገር አስተያየት ለመስጠት አልችልም።“ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ኮሪያው አምበል ኪ ሱንግ ዩንግ በበኩሉ “ኮሎምቢያዎች ሲጫወቱ የነበሩት ጠንካራ እና በአካላዊ ንክኪ ላይ ያደረገ እንቅስቃሴ ነበር።ይህም በእግርኳስ የሚያጋጥም ነው።ነገርግን የዘረኝነት ስድብ በፍፁም ተቀባይነት የለውም።ኮሎምቢያ ምርጥ ተጫዋቾች ያላት አገር በመሆኗ ይህን ነገር በመመልከቴ ተከፍቻለው።” በማለት ስሜቱን ገልጿል።

ኮሎምቢያዊያን ጭምር በተጫዋቹ ላይ ጠንካራ ቅጣት ሊተላለፍለት እንደሚገባ እየተነገረ ባለበት ወቅት ተጫዋቹ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ በመጠየቅ ውዝግቡን ረገብ ለማድረግ ሞክሯል።

በብሔራዊ ቡድኑ የትዊተር አካውንት በኩል በቪድዮ መልእክቱን ያስተላለፈው ኤድዊን ካርዶና “ያደረኩት ሆን ብዬ ሌላ ሰውን፣ሀገርን እና ዘርን ላለማክበር አይደለም።ነገርግን ማንም ሰው እንደዛ አድርጎ ከተረጎመው ይቅርታ እጠይቃለው።”ሲል በይፋ ይቅርታውን አቅርቧል።

እንደ ኮሪያው የዜና አውታር ዮንሀፕ ደግሞ የኮሎምቢያ እግርኳስ ማህበር በተጫዋቹ ጥፋት በመፀፀት ይቅርታ መጠየቃቸውን ገልጿል።

ፊፋ ዘረኝነትን እና የመድሎ ልዩነቶችን ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር በታዋቂ ተጫዋቾች እና በሌሎች መንገዶች “Say No to Racism” በማለት እያደረገው የነበረው ዘመቻ በመቀጠል  ሁሉም አካላቶች ያላሳለሰ ትብብር በማድረግ ዘረኝነትን ከስፓርታዊ መድረኮች ለማጥፋት መዋጋት ይኖርባቸዋል።

Advertisements