ጣሊያን አሰልጣኟን ጂያንፔሮ ቬንቹራን አሰናበተች!

ከ1958 የዓለም ዋንጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአለማችን ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ መድረስ የተሳናት ጣልያን ለዚህ ውድቀት ተጠያቂ ያለቻቸውን የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ቬንቹራን አሰናብታለች፡፡

ከስውዲን ጋር ባደረገችው የደርሶ መልስ ማጣሪያ በድምር ውጤት 1 ለ 0 በመሸነፍ የሩሲያውን የአለም ዋንጫ በሩቁ ለመመልከት የተገደደችው ጣልያን ከውጤቱ በኋላ እግር ኳሷ በከፍተኛ ሁኔታ የታመሰ ሲሆን የቡድኑን አምበል ጂጂ ቡፎንን ጨምሮ በርካታ አንጋፋ ተጫዋቾቿ ራሳቸውን ከአዙሪዎቹ እንዲያገሉ ከውሳኔ አድርሷቸዋል፡፡

 ይህንን ውጤት ተከትሎ የጣልያን እግር ኳስ ማህበር አሰልጣኙን ለመቀየር እንዳሰበ ሲወራ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ይፋ ባደረገው መልዕክቱ አሰልጣኙን ለማሰናበት መወሰኑን ገልጿል፡፡

የአሰልጣኙን ስንብት ተከትሎ አዙሪዎችን ከመረከብ ጋር በርከት ያሉ አሰልጣኞች ስማቸው እየተያያዘ ቢገኝም ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ ከቀድሞው የኤሲ ሜላን ፣ የቼልሲ ፣ የሪያል ማድሪድና የባየርን ሙኒክ ውጤታማ አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ጋር ንግግር መጀመሩ ተሰምቷል፡፡

ጣልያን ለ 2020ው የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ጅማሮ በፊት በቀጣዩ መጋቢት ወር ከእንግሊዝና ከአርጀንቲና ጋር የወዳጅነት ጨዋታዋን ታደርጋለች፡፡

Advertisements