ፍቺ / ማንችስተር ዩናይትድ ማርዋን ፌላኒን በነፃ ሊያጣ እንደሚችል ተነገረ

ማርዋን ፌላኒ ባሳለፍነው መስከረም የቀረበለትን የውል ማራዘሚያ ስምምነት ለመፈረም ፍቃደኛ ሳይሆን ከመቅረቱ ጋር በተያያዘ ማንችስተር ዩናይትድ ቤልጄማዊውን አማካኝ በመጪው ክረምት የሚያጣበት ዕድል ሊፈጠር እንደሚችል ተነግሯል። 

የኦልትራፎርዱ ክለብ ካሳለፍነው የውድድር ዘመን አንስቶ የፌላኒን የውል ስምምነት ለማራዘም በድርድር ላይ ቢቆይም ተጫዋቹ በቀረበለት ጥቅማ ጥቅም ደስተኛ አለመሆኑ ድርድሩ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆኗል።

ቤልጄማዊው ቁመተ መለሎ ባሳለፍነው ጥር የአንድ አመት የውል ማራዘሚያ ስምምነት ዩናይትድ ሲያቀርብለት ደሞዙ በሳምንት ከ 80,000  ፓውንድ ወደ 120,000 ፓውንድ እንደሚያድግለት ታስቦ የነበረ ቢሆንም ፌላኒ ትልቅ የደሞዝ ማሻሻያን መፈለጉ ነገሩን አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል። 

በሌላ በኩል ግን የተጫዋቹ ግትር አቋም እንዳለ ቢሆንም አጥብቆ ፈላጊው ጆሴ ሞውሪንሆ እስከ መጪው ጥር ድረስ ከእሱ ጋር የሚካሄዱ ድርድሮች ካልተሳኩ ተጫዋቹ እንዳይሸጥ ማድረግ የሚችሉበት አቅም አይኖራቸውም።   

ምክንያቱም ፌላኒ በመጪው ክረምት ከዩናይትድ ጋር ያለው ቆይታ የሚጠናቀቅ መሆኑና የኦልትራፎርዱ ክለብ አፋጣኝ የውል ማራዘሚያ ስምምነት ማድረግ የሚያስችለው አማራጭ በውሉ ላይ የሌለ መሆኑ የቀድሞው የኤቨርተን ኮከብ በመጪው ጥር ከፕሪምየር ሊጉ ውጪ ካለ ማንኛውም ክለብ ጋር የቅድመ ውል ስምምነት መፈራረም ያስችለዋል። 

የተጫዋች የውል ስምምነት ደንብ እንደሚለው ከሆነም ማንኛውም ተጫዋች የውል ስምምነቱ ከመጠናቀቁ ስድስት ወራት ቀደም ብሎ የዝውውር ቅድመ ስምምነት ማድረግ መቻሉም ለፌላኒ የቅድመ ውል ስምምነት መፈራረሚያ ነፃነትን ይሰጠዋል። 

ፌላኒ በ 2013 ክረምት በ 27.5 ሚሊዮን ፓውንድ በዘመነ ዴቪድ ሞይስ ወደ ኦልትራፎርድ ከመጣ በኋላ አስቸጋሪ ጊዜያት አሳልፎ በሞውሪንሆ ስብስብ ውስጥ ቁልፍ ሚና ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ ሆኖ ብቅ ማለት የቻለ ነው። 

ፖርቹጋላዊው የኦልትራፎርድ አለቃም በክለቡና በአማካኙ መሀከል ያለው የውል ስምምነት መካረር ተለሳልሶና አዲስ የውል ማራዘሚያ ስምምነት ተደርጎ ፌላኒ በቡድኑ እንዲቆይ ትልቅ ፍላጎት አላቸው። 

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በቀጣዩ ሳምንት 30ኛ እድሜውን የሚደፍነውን ተጫዋች ዩናይትድ በቀጣዩ ክረምት ያለምን ቤሳቤስቲ በነፃ ለማጣት ይገደዳል።

Advertisements