ማንሰራራት / ዝላታን ኢብራሂሞቪች ከጉዳት መልስ በአዲስ ሚና ወደሜዳ ለመመለስ እንደሚፈልግ ፍንጭ ሰጠ

የማንችስተር ዩናይትዱ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ ወደሜዳ ሲመለስ በ 10 ቁጥር ሚና እንደሚሰለፍ ፍንጭ ሰጠ። 

የ 36 አመቱ ግዙፍ አጥቂ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ለኦልትራፎርዱ ክለብ 28 ያህል ግቦችን በማስቆጠር በኮከብ ግብ አግቢነት ቢያጠናቅቅም በወርሀ ሚያዚያ በኢሮፓ ሊግ ሩብ ፍፃሜ የደረሰበት የጉልበት ጅማት መበጠስ ለወራት ከሜዳ ውጪ ያደረገው ሲሆን ይለብሰው የነበረውን ዘጠኝ ቁጥር መለያም አጥቷል። 

ስዊድናዊው አጥቂ ይለብሰው የነበረውን መለያ ለሮሜሉ ሉካኩ ቢሰጥበትም ከዋይኒ ሩኒ መልቀቅ ጋር በተያያዘ የተረከበውን 10 ቁጥር መለያ በመልበስ ከፊት አጥቂነት ሚና ይልቅ መደበኛውን የ 10 የጨዋታ አቀጣጣይነት ቁጥር ሚና ይዞ መጫወት እንደሚያስደስተው ገልጿል።

ኢብራሂሞቪች ጉዳዩን ሲያስረዳም “ለእኔ 10 ቁጥር ኮከብ ነው። እሱ ልዩነት የሚፈጥረው፣  እይታ ውስጥ የሚገባ፣ ጨዋታዎችን የሚያሸንፍ እና መሪ ነው። እኔም እራሴን በዛ ቦታ ላይ አድርጌ የምመለከት ቢሆንም የምትሆነው እንጂ ለአንተ በችሮታ መልክ የሚሰጥህ አይደለም። ነገሩ እንደዛ ነው።

“እውነት ለመናገር ነገሩ ከጉዳት እንዳገግም መነሳሻ ነው። ምክንያቱም በስዊድን ብሔራዊ ቡድን እና በፒኤስጂ 10 ቁጥርን ለብሻለሁ። በኢንተርም ለብሼው የነበረ ሲሆን ነገርግን በቶሎ ወደ ባርሴሎና አመራሁ።

“እሱን በሚላን ፈልጌው ነበር። ነገርግን ከክብር የተነሳ ሌላ ቁጥር ተቀበልኩ። በአያክስ አልለበስኩትም። በዛ እንደ 10 ቁጥር ተጫዋች ይሰማኝ የነበረ ሲሆን ለዛ የቆምኩ ነበርኩ። በታሪክ ውስጥ ሁሌም በ 10 ቁጥር ሚና መጫወቴ የሚነገርልኝ ነኝ።” በማለት ተናግሯል።

ከስዊድናዊው ኮከብ ጉዳት በተያያዘ ሌላ መረጃ አንዳንድ ሪፖርቶች ዝላታን በመጪው ቅዳሜ ለሚደረገው ጨዋታ ሊደርስ እንደሚችል እየጠቆሙ ሲሆን ጆሴ ሞውሪንሆ በበኩላቸው አጥቂያቸው ይህ የፈረንጆቹ አመት ከመጠናቀቁ በፊት ወደሜዳ እንደሚመለስ ተናግረዋል።

Advertisements