ከአሳፋሪ ቆይታቸው በኋላ ማርክ ዊልሞትስ ከአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን ሀላፊነታቸው ተነሱ


በ ዕዮብ ዳዲየአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ቤልጄማዊው ማርክ ዊልሞትስ በስድስት ወራት ውስጥ አሰቃቂ ውጤት አስመዝግበው ከአይቮሪኮስት እግርኳስ ማህበር ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በጋራ ስምምነት ከሀላፊነታቸው ተነስተዋል።

ዊልሞትስ ወርቃማው ትውልድ የተባለለት የቤልጄም ብሔራዊ ቡድንን በዩሮ 2016 ይዘው ቀርበው ዋንጫ ሲጠበቅባቸው ባልታሰበ መልኩ በዌልስ ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ ሲሆኑ ቁጥር ስፍር የሌለው ትችቶችን ማስተናገዳቸው ይታወሳል።

ለትችት ያጋለጣቸው ደግሞ ከውድድሩ መሰናበታቸው ብቻ ሳይሆን በትውልድ ሊተካ እንደማይችል እየተነገረ የሚገኘው በከዋክብት ተጫዋቾች የተጥለቀለቀው የቤልጄም ብሔራዊ ቡድንን ይዘው ያላቸውን የተጫዋቾቻቸውን አቅም ሊጠቀሙበት አለመቻላቸው ነበር።

ጠንካራ ቡድን መገንባት ከብዷቸው ስማቸው ባነሰ የአውሮፓ ቡድኖች ሲፈተኑ ከቆዩ በኋላ በብሔራዊ ቡድኗ የገነነ ስም በሌላት በክሪስ ኮልማን ይመራ በነበረው ዌልስ በሩብ ፍጻሜ 3-1 ተሸንፈው ከ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ተሰናብተው ወደ ሀገራቸው ተሰናበቱ።

በወቅቱ ክሪስ ኮልማን በግማሽ ፍጻሜው ከፖርቹጋል ጋር ከደረሳቸው በኋላ ዌልስ ከ 1958 የአለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በብራዚል ከተሸነፈች በኋላ የምታደርገው ጠንካራ ጨዋታ ነው በማለት ሲናገሩ ማርክ ዊልሞትስ በበኩላቸው ወደ ሀገራቸው ቤልጄም ሲመለሱ በአውሮፓ ዋንጫው ላይ ባሳዩት ደካማ ብቃት የስንብት ደብዳቤ ተፅፎ ጠብቋቸዋል።

በ 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ከምድቧ ማለፍ የተሳናት አይቮሪኮስት ሚሼል ዱስየርን ካሰናበተች በኋላ አይኗን ወደ ማርክ ዊልሞትስ በማድረግ የሁለት አመት ኮንትራት አቀረበች።

መጋቢት 2017 ላይ ቤልጄማዊው አሰልጣኝ “ዝሆኖቹን” ለማሰልጠን በወር 50ሺ ዶላር ሊከፈላቸው በመስማማት ፊርማቸውን ያኖሩ ሲሆን ቡድኑን ለ 2018 የአለም ዋንጫ ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ የመጀመሪያ እቅዳቸው እንዲሆን ተነግሯቸው ነበር።

ለአለም ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የማጣሪያ  ጨዋታ ከጋቦን፣ሞሮኮ እና ማሊ ጋር ተደልድላ የነበረችው አይቮሪኮስት ዊልሞትስን ስትቀጥር በአራት ነጥብ ምድቧን ትመራ የነበረ ሲሆን ከቤልጄም ጋር ውጤታማ ቆይታ ማድረግ የተሳናቸው ዊልሞትስ ዝሆኖቹን የምድብ መሪነት አስጠብቀው በአለም ዋንጫው ላይ እንዲሳተፉ ስለማድረጋቸው የተጠራጠሩ በርካቶች ነበሩ። 

እንደተሰጋውም አሰልጣኙ ባለፉት ስድስት ወራት የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድንን ትንሽ አድርገውት ታይተዋል።ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ ማሸነፍ የቻሉት አንዱን ብቻ ሲሆን፣በአንድ ጨዋታ አቻ ወጥተው በአራቱ ደግሞ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።

የሚገርመው ቡድናቸው ከተሸነፋቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ ሶስቱ በሜዳቸው ያደረጉት ጨዋታ ሲሆን ይህም ቆይታቸው በስድስት ወራት ብቻ እንዲገደብ በር ከፍቷል።

ከቀናቶች በፊት ለአለም ዋንጫ ለማለፍ ሞሮኮን ማሸነፍ ይጠበቅባቸው የነበሩት ዝሆኖቹ በወሳኙ ጨዋታ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት በቀድሞ አሰልጣኛቸው ሄርቬ ሬናልድ ይመሩ በነበሩት ሞሮኮዎች ተሸንፈዋል።

ሽንፈቱም አይቮሪኮስቶች በተከታታይ ከተሳተፉበት የአለም ዋንጫ ውጪ እንዲሆኑ ሲያደርጋቸው ከአሰልጣኙ ቤልጄማዊው ማርክ ዊልሞትስ ደግሞ ደካማ የስድስት ወራት ቆይታቸው ፍጻሜው ሆኗል።

የአይቮሪኮስት የእግርኳስ ማህበር ከውጤቱ በኋላ ከአሰልጣኙ ጋር ውይይት በማድረግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከግብ ባለማድረሳቸው በስድስት ወራት 300 ሺ ዶላር ከከፈሉት አሰልጣኝ ጋር በጋራ ስምምነት መለያየታቸውን ይፋ አድርገዋል።

አሰልጣኙም በትዊተር ገጻቸው ላይ ለነበራቸው ቆይታ የቡድኑ አባላት፣የሀገሪቷ የእግርኳስ አስተዳዳሪዎችን እና ደጋፊዎችን በሙሉ ምስጋና አቅርበው ተሰናብተዋል።

Advertisements