የመድፈኞቹ አለቃ አርሴን ዌንገር ስለ ሳንቲ ካርዞላ የጉዳት ሁኔታ ተናገሩ

በሰሜን ለንደን የደርቢ ጨዋታ ቅዳሜ ከቶተንሀም ጋር ጠንካራ ጨዋታ ያለባቸው አርሰን ዌንገር በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ጉዳት ላይ ስለሚገኘው ስፔናዊው አማካይ ሳንቲ ካርዞላ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በአርሰናል ደጋፊዎች የሚወደደው ስፔናዊው አማካይ ከሜዳ ከራቀ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ከጉዳቱ አገግሞ ቶሎ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም እንደታሰበው ሳይሆን ጉዳቱ ከፍቶበት ቆይቷል፡፡

የ 32 አመቱ ተጫዋች ለመጨረሻ ጊዜ ለአርሰናል የተጫወተው በቻምፒየንስ ሊጉ ከሎዶጎሪትስ ጋር በጥቅምት 2016 ላይ ሲሆን በጨዋታው ላይም ጉዳት አጋጥሞት እንደነበር ይታወሳል።

ተጫዋቹ ያጋጠመው የተረከዝ ጉዳት ለስምንት ያህል ጊዜ ቀዶ ጥገና እንዲያደርግ ያስገደደው ሲሆን በአንድ ወቅት ዶክተሮች ከአሁን በኋላ ቆሞ መራመድ የሚችል ከሆነ እድለኛ እንደሆነ ነግረውታል፡፡

ጉዳት ያጋጠመው የሳንቲ ካርዞላ እግር

በቅርቡ ከስፔኑ ማርካ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ያደረገው ካርዞላ ስለ ጉዳቱ አስከፊነት ተናግሯል፡፡ ተረከዙ ወደ ኢንፌክሽን ተቀይሮ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ከክንዱ ላይ ሌላ ቆዳ ተወስዶ እንደተሰራለትም በመናገር አሁን ግን በጥሩ ስሜት ላይ መሆኑን ለማርካ ጋዜጣ መናገሩ ይታወሳል፡፡

አርሰን ዌንገር ተጫዋቹ በጥር ወር ላይ እንደሚመለስ በማሰብ 25 ተጫዋቾችን ካስመዘገቡበት የፕሪምየርሊግ ቡድን ዝርዝራቸው ውስጥ ባያካትቱትም ጉዳቱ ግን እስከዛሬ በአሰልጣኝነት ቆይታቸው አይተውት የማያውቁት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ጉዳቱ በህይወቴ ካየኋቸው ውስጥ አስከፊው ነው፡፡ሲጀምር ተረከዙ ላይ ህመም ነበር ከዛም እየባሰ ሄደ፡፡ሳንቲ ምን ያህል ኳስ መጫወት እንደሚወድ አውቃለው በሱ ላይም ስለሆነው ነገር በጣም አዝናለው፡፡ምክንያቱም ጉዳቱ የማይታመን ነው፡፡እዚህ ስለነበር ያየሁት ከአንድ ወር በፊት ነው፣ የቻለውን ያህልም እንዲዘጋጅም ነግሬዋለው፡፡

ሳንቲ ካርዞላ

“በሱ አካባቢ ጥሩ የሆኑ ህክምና ሰዎች አሉ። ስለዚህ ሜዳ ለመመለስ መለማመድ ይኖርበታል፡፡በቅርቡ ግን አላገኘሁትም፣ ነገርግን እንደሚመለስ ተስፋ አደርጋለው፡፡ከቡድኑ የፕሪምየርሊግ የቡድን ዝርዝር ውስጥም ያወጣሁት በጥር ላይ እንደሚመለስ በማሰብ ነው፡፡”

ተጫዋቹ ተመልሶ መጫወት የመቻሉ ጉዳይ አጠራጣሪ ስለመሆኑ የተጠየቁት አርሴን ዌንገር ሲመልሱ “ስለዛ ነገር አናውራ፤ እናንተ እያወራችሁ ያላችሁት የተሳሳተ ነገር ነው፡፡” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ካርዞላ በቅርቡ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚያሳይ ቪድዮ በመልቀቅ “እግርኳስን በድጋሜ በጥሩ ሁኔታ መጫወት እንደምችል እምነት አድሮብኛል።”የሚል መልእክት አስተላልፏል።

Advertisements