አልማዝ አያና ለመጀመሪያ ጊዜ የምትሳተፍበት የደልሂ ግማሽ ማራቶን እሁድ ይካሄዳል

የ10,000 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ኢትዮጵያዊ አትሌት አልማዝ አያና የመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎዋን የምታደርግበት የህንዱ ደልሂ ግማሽ ማራቶን ውድድር የፊታችን እሁድ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ደልሂ ግማሽ ማራቶን አይርቴል በተባለው ኩባንያ ስፖንሰር የሚደረግ ሲሆን ከአልማዝ በተጨማሪም የ2017 የለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ጂዮፍሪ ኪሩይ በወንዶቹ ውድድር ተሳታፊ ይሆንበታል፡፡
ሁለቱ ታላላቅ አትሌቶች ውድድሩን አሰመልክቶ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የስፍራውን ክብረወሰን ለማሻሻል እንደተዘጋጁ የተጠየቁ ሲሆን ሁለቱም በተመሳሳይ በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኙ እና ለዚህ ውድድር ምርጥ አቋም ላይ ባይገኙ ኑሮ እንደማይሳተፉ ጭምር ተናግረዋል፡፡

በተለይ አልማዝ ከአለም ሻምፒዮኗው በኋላ ምንም አይነት ውድድር ሳታደርግ ለዚህ ፍልሚያ ስትዘጋጅ መቆየቷን ተናግራለች፡፡ አትሌቷ እንዳለችው “የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ካሸነፍኩ በኋላ ሌላ ውድድር አላደረኩም ፤ ብዙም ጥሩ ውድድሮች ስላልነበሩ በርትቼ ለዚህ ማራቶን ልምምዴን ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ በእርግጥ የማራቶን ውድድር የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ውድድር ነውና ለማሸነፍ ነው የምገባው፡፡”

አልማዝ ቀጥላም “ግማሽ ማራቶንን ሮጥኩ ማለት ከመም ውድድሮች ራሴን ላርቅ ነው ማለት አይደለም ፤ አሁንም ትኩረቴ መም ላይ ነው፡፡ የደልሂ ማራቶንን ከሮጥኩ በኋላ በድጋሚ ማራቶኖችን መሮጥ እንዳለብኝ እወስናለሁ፡፡ ” በማለት አጠቃላለች፡፡

የህንዱ ደልሂ ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በወንዶቹ  በኢትዮጵያዊው ጉዬ አዱላ(59:06) የተያዘ ሲሆን የሴቶቹ ደግሞ በኬንያዊቷ ሜሪ ኪታኒ (1:06:54) ተይዟል፡፡

የደልሂ ግማሽ ማራቶንን በአሸናፊነት መጨረስ 27 ሺህ ዶላር ሽልማትን እንደሚያስገኝም የደረሰን ማስረጃ ያሳያል፡፡

Advertisements