ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሙያው እና በግል ህይወቱ ዙሪያ የወደፊት እቅዱን አሳወቀ

12

አምስተኛውን የባሎንዶር ሽልማት በቀጣይ ወር እንደሚያሳካ እየተጠበቀ የሚገኘው ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በቀጣይ አመታት በእግርኳስ  እንዲሁም በግል ህይወቱ ዙሪያ ሊያሳካው የሚፈልገውን እቅዱን አሳውቋል፡፡

ከሪያል ማድሪድ ጋር የቻምፒየንስ ሊግ በአዲስ መንገድ መካሄድ ከጀመረ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ አመታት ባለ ትልቁን ዋንጫ ማንሳት የቻለው ሮናልዶ 2016/2017 ውጤታማ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል፡፡የስፔን ላሊጋንም ከባርሴሎና የበላይነት ነጻ ማውጣት የቻሉበት አመት ነበር፡፡

ይህ ስኬቱ በቀጣዩ ወር ይፋ ለሚደረገው የፊፋ ባሎንዶር ሽልማት ቅድሚያ እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ሽልማቱን ካሸነፈ ደግሞ ከሌላው ተቀናቃኙ ሊዮ ሜሲ እኩል አምስት ጊዜ በማሸነፍ ሪከርዱን የሚጋራ ይሆናል፡፡

ሮናልዶ ከሰሞኑን አፈትልከው የወጡ መረጃዎች መሰረት ሊዮ ሜሲ የባሎንዶሩን አሸንፊ መሆኑን የሚገልጹ በመሆኑ ትንሽ ስጋት ሳያድርበት አልቀርም፡፡ነገርግን ተጫዋቹ ጉዳዩን አጣርቶ የ 2017 የባሎንዶር አሸናፊ የሆነው እራሱ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡ይህንንም ለሊዮ ሜሲ ደውሎ እንዳሳወቀ አንድ ስፔን ድረ ገጽ መረጃ ይዞ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን አንጂ በዘንድሮ የላሊጋ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ አጀማመሩ መልካም አልሆነም፡፡አንድ ጎል ብቻ በማስቆጠር ትችቶች እየቀረቡበት ይገኛሉ፡፡በተቃራኒው ሜሲ ደግሞ 12 ጎሎችን በማስቆጠር አጀማመሩን አሳምሯል፡፡

14

እነዚህ ጉዳዮች እየተናፈሱ ባሉበት ወቅት ሮናልዶ በሙያው እንዲሁም በግል ህይወቱ ዙሪያ እቅዱን ይፋ አድርጓል፡፡በግል ህይወቱ አራተኛ ልጁን ባለፈው ሳምንት ያገኘ ሲሆን በአጠቃላይ ሰባት ልጆች እንዲኖሩት ይመኛል፡፡

“አሁን እኔ አካባቢ ብዙ ሰዎች ስላሉ ደስተኛ ነኝ፡፡ልጆች እንዲኖሩኝ እፈልጋለው፡፡ለኔ ህይወት ካለ ልጆች ምንም ነው፡፡”ሲል ስለ ቤተሰቡ ተናግሯል፡፡

በእግርኳስ ህይወቱ ደግሞ ጫማ ከመስቀሉ በፊት ለሰባት ጊዜያት የባሎንዶር አሸናፊ መሆን እንደሚፈልግ ይፋ አድርጓል፡፡ከፈረንሳዩ ሌኪፕ ጋር ቆይታ ያደረገው ሮናልዶ “መጫወቴን እስከቀጠልኩኝ ድረስ የምችላቸው ነገሮች ሁሉ ማሸነፍ እፈልጋለው፡፡አሁን ህልሜ አምስተኛው ባሎንዶርን ማሸነፍ ነው፡፡ከዛም ለቀጣዩ አመት ደግሞ ለሌላ ክብር እፋለማለው፡፡” ሲል ተናግሯል፡፡

ሪያል ማድሪድ ከባርሴሎና ጋር ያለው ልዩነት ስምንት ደረሰ ሲሆን ቅዳሜ ምሽት ላይ ደግሞ ከከተማው ተቀናቃኝ የሆነው አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ጠንካራ ጨዋታ ይጠብቀዋል፡፡ከጨዋታውም ማድሪዶች የግድ ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህ ካልሆነ እና ባርሴሎና በድል መወጣት የሚችል ከሆነ ከወዲሁ በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለው ነጥብ ሊራራቅ ይችላል፡፡

ሮናልዶ ግን የዋንጫ እድላቸውን ማሻሻል እንደሚገባቸው እምነቱ አለው፡፡“እኛ ባለፉት ሁለት አመታት የቻምፒንስ ሊግ አሸናፊዎች ነን፡፡የላሊጋም የባለፈው አመት ባለድል ነን፡፡ይህ ደግሞ ሊከበር ይገባዋል፡፡አሁንም እራሳችን ለማሻሻል ዝግጁዎች ነን፡፡”በማለት ስለ ቡድኑ ጨምሮ ተናግሯል፡፡

 

Advertisements