ኢላማ / ማንችስተር ዩናይትድ ጋሬዝ ቤል ጉዳት ቢደጋገምበትም አሁንም አጥብቆ ፈላጊው እንደሆነ ተገለፀ 

ፅሁፍ ዘገባ : በሚኪያስ በቀለ

ማንችስተር ዩናይትድ ጋሬዝ ቤልን ከሪያል ማድሪድ የማስፈረም ትልቅ ፍላጎት አሁንም እንዳለው እየተነገረ ሲሆን የተጫዋቹ የጉዳት መደጋገም እንደማያሳስበውም ተያይዞ ተገልጿል።   

ቤል ከጉዳት ጋር በተያያዘ ከማድሪድ ያለፉት 60 ጨዋታዎች 40 ያህሉ ያመለጡት ሲሆን ከመስከረም መጨረሻ አንስቶም ምንም አይነት ጨዋታ አላደረገም። 

ዌልሳዊው ኮከብ አምና ከገጠመው የባት ጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ሲያገግም ባሳለፍነው ሳምንት የገጠው የብሽሽት ጉዳት ደግሞ ለተጨማሪ አንድ ወር ከግማሽ ከሜዳ እንደሚያርቀው ተገምቷል።

ይህ አዲስ ጉዳትም ቤል በጊዜው የአለም ሪከርድ ዋጋ በ 2013 በ 85 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ማድሪድ ከመጣ አንስቶ የገጠው 19ኛ ጉዳቱ ቢሆንም ዩናይትድ ተጫዋቹን ከመፈለግ አላገደውም። 

ከዚህ ቀደም ወደ ኦልትራፎርድ ሊያመጡት ፍላጎት የነበራቸው የኦልትራፎርዱ ፖርቹጋላዊ አለቃ ጆሴ ሞውሪንሆም ተጫዋቹን ከመጪው ክረምት በፊት ለማምጣት መሞከር የማይቻል ቢመስልም በዌልሳዊው ላይ ያላቸው ፍላጎት አሁንም ከፍተኛ ነው። 

ዩናይትድም ቤል በቶትነሀም ቤት በነበረው የበዛ የመሰለፍ ሪከርድ የተበረታታ ሲሆን ዌልሳዊውን ኮከብ በእጁ ማስገባት የሚችል ከሆነም በኋይት ሀርትሌን ወደነበረው የመሰለፍ አቋሙ እንደሚመልሰውም ትልቅ ተስፋ ሰንቋል።

ቤል ወደ ማድሪድ ከማምራቱ በፊት በነበረው የውድድር ዘመን በስፐርሶች ቤት 52 ጨዋታዎችን ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ከዛ ቀደም በነበረው አመት 48 እና በ 2010-11 ደግሞ 44 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል። 

ቤል በበርናባው ከግብር በኋላ የተጣራ 350,000 ፓውንድ ሳምንታዊ ደሞዝ የሚያገኝ ሲሆን በስፔኑ ክለብም እስከ 2022 የሚያቆየው የውል ስምምነት አለው። 

ዌልሳዊው ኮከብ ውል ማፍረሻው አንድ ቢሊዮን ፓውንድ (890 ሚሊዮን ፓውንድ) ቢሆንም ካለው የጉዳት መወሳሰብ አንፃር ማድሪድ በአነስተኛ ገንዘብ እንደሚሸጥውም ይጠበቃል። 

Advertisements