የቅድመ ጨዋታ ትንታኔ / አትሌቲኮ ማድሪድ ከ ሪያል ማድሪድ

በዚህ በሳምንቱ ተጠባቂ የላሊጋ ፍልሚያ ከስፔን የመናገሻ ከተማ ማድሪድ ወጣ ብሎ የከተመው አትሌቲኮ ማድሪድ 68,000 ተመልካች በሚይዘው ግዙፉ ዋንዳ ስታዲየም የዋና ከተማው እምብርት ላይ የሚገኘውን የምንግዜም ተቀናቃኙን ያስተናግዳል። 

ቀጣዩ የሚኪያስ በቀለ የቅድመ ጨዋታ ትንተናም ከሊጉ መሪ ባርሴሎና በስምንት ነጥቦች ርቀት በተመሳሳይ 23 ነጥብ ላይ የተቀመጡትን እና በ 162ኛው የእርስ በርስ የሊግ ፍልሚያ የሚገናኙትን የሁለቱን ቡድኖች ትንቅንቅ እንደሚከተለው ያስቃኘናል። 


                      

                       አጠቃላይ ግምገማ

አትሌቲኮ ማድሪዶች በዚህ ሳምንትም ለጎረቤታቸው እጅ የማይሰጡ ከሆነ በሊጉ ላይ ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን በትልቁ የሚቀጥሉ ይሆናል። 

ነገርግን ከላይ ያለው ክብረ ወሰን ብቻ ሙሉ ታሪኩን አይገልፅም። ምክንያቱም በዝውውር እገዳ ውስጥ ክረምቱን ማሳለፋቸውና ቡድናቸውን ለማጠናከር የነበራቸው ተስፋም አዲስ ያስፈረሟቸውን ዲያጎ ኮስታንና ቪቶሎን ከመጪው ጥር በፊት መጠቀም ካለመቻላቸው ጋር ተደማምሮ በሊጉ ካደረጉት 11 ጨዋታ አምስቱን በአቻ ውጤት በመፈፀም በአምስተኛ ደረጃ አሽቆልቁለው እንዲቀመጡ አስገድዷቸዋል። 

በውድድር ዘመኑ በሊጉ ሽንፈት ካልገጠማቸው ሶስት ቡድኖች አንዱ መሆን ጥሩና አመርቂ ግስጋሴ ቢሆንም ዲያጎ ሲሞኔ ከ 2014 አሸናፊነት በኋላ ዳግም በሊጉ ላይ ለመንገስ ጨዋታዎችን መግደልና ሙሉ ነጥብ ይዞ ከመውጣት ውጪ አማራጭ እንደሌለ ያውቁታል።

አትሌቲኮ በሁሉም ውድድሮች ላይ ካለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ብቻ ሲሆን ያስቆጠረው ግብም በየጨዋታው አንድ ያህል ወይም በአጠቃላይ ሰባት ጎሎችን ብቻ መሆኑ ገና በጊዜ ከአራቱ የሊጉ መሪዎች ውጪ ሆኖ መቀመጡ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ጭምር እንዳያሳጣው አስግቷል። 

ብዙ የክለቡ ደጋፊዎች እንደፈሩትም ወደአዲሱ ስታዲየም የተደረገው ሽግግር በአዲሱ የውድድር ዘመን ዋጋ እያስከፈላቸው የሚገኝ ሲሆን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ቪያሪያል እና ባርሴሎና በመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ግብ አስቆጥረው በዋዳ ስታዲየም ነጥብ ከወሰዱ መሀከል ይገኛሉ። 

በአጠቃላይ ሲታይ የአትሌቲኮ የውድድር ዘመን ጅማሬ በጣም አስከፊ የሚባል አይነት ባይሆንም በላሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ በመቀመጥ ውጣውረድ ውስጥ ሆኖ የቆየው የሲሞኔ ስብስብ ያለፉት ሳምንታት ሂደት ከማድሪድ ጋር በነጠብ እኩሌታ ላይ ሆኖ የደርቢውን ጨዋታ እንዲጠብቅ ሲያደርገው በዛሬው ምሽት ጨዋታ የሚኖረው ውጤትም የሁለቱን የዋና ከተማ ክለቦች ቀጣይ ሂደት በመወሰን ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የሚጠበቅ ነው።  

በሌላ ተያያዥ መረጃ የክለቡ ፕሬዝዳንት ኤንሪክ ሴሬዞ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ሲሞኔ በአትሌቲኮ ቤት “የማይነካ” እንደሆነ ቢናገሩም የአጨዋወቱ መንገድ የወረደው የስፔናዊው አለቃ ስብስብ በቀጣይ ከሚጠበቀው በታች ውጤት ማስመዝገቡን የሚቀጥል ከሆነ የኢሮፓ ሊግ፣ ኮፓ ዴላሬይና የላሊጋው አሸናፊ ሲሞኔ የአሰልጣኝነት ወንበራቸው ላይ ጫና እንደሚፈጠር የሚጠበቅ ነው።  

በሌላ በኩል የአሰልጣኝነት ጊዜውን ሁለተኛ የውድድር ዘመን ላይ የሚገኘው ዚነዲን ዚዳን በሽንፈት ካጠናቀቀው ጨዋታዎች ይልቅ በበርናባው ያነሳቸው ዋንጫዎች ቁጥር ብልጫ አላቸው። 

በዚህ ሁሉ መሀከል ግን ሰባት ትልልቅ ዋንጫዎችን ለዋና ከተማው ያስገኘው የዚዳን ስብስብ ከተጀመረ ሶስተኛ ወሩ ላይ በሚገኘው የ 2017/18 የውድድር ዘመን ላይ የመንሸራተት ምልክቶችን እያሳየ ሲሆን በሁሉም ውድድሮች ላይ ካደረገው 15 ጨዋታዎችም በሶስቱ ሲሸነፍ ሁለቱን በአቻ ውጤት ለመጨረስ ተገዷል።

ማድሪድ ዘንድሮ ካጋጠመው መንሸራተትም በጥቂት ቀናት ልዩነት በተከታታይ በጂሮና እና ቶትነሀም የደረሰበት ሽንፈት ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን ፈረንሳዊው የክለቡ ቆፍጣና አለቃ ግን ከሁለት ሳምንት በፊት ላስ ፓልማስን ከመግጠማቸው በፊት ቡድኑ ምንም አይነት “ፈተና” እንዳልገጠመው በመናገር ነገሮችን ለማርገብ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል።  

በዚህም ተባለ በዚያ ግን የዚዳን ስብስብ የቆመበት ይህ ሰአት በቀጣይ ከገና እረፍት በፊት ስድስት የሊግ ጨዋታ፣ ሁለት ወሳኝ የቻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያዎች፣ የኮፓ ዴላሬይ እና የአለም የክለቦች ዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲያደርግ ከሚያስገድደው እረፍት አልባ ሁለት ወራት በፊት የሚገኝ ወሳኝ ማሰቢያ ወቅት ነው። 

ማድሪድ ከእነዚህ ከፊቱ ከቆሙት ፍልሚያዎችም በወርሀ ታህሳስ አጋማሽ በኤልክላሲኮው ትንቅንቅ ከምንግዜው ባላንጣው ባርሴሎና የሚገናኝበት መሆኑ ሁሌም የስንብት ውሳኔ ለማሳለፍ ትንሽ በሚበቃው የዋና ከተማው ክለብ ውስጥ የዚዳን የቀጣዮቹ ሁለት ወራት የመቀጠልና ከመንገድ የመቅረት ያህል ወሳኝነት ያላቸው ናቸው።  

ከዚህ ጋር በተያያዘም ዚዳን የተቃጣበትን የመሰናበት ስጋት አልፎ አንገቱን በኩራት ብቅ ለማድረግ ከዛሬ ምሽቱ የደርቢ ትንቅንቅ አንስቶ ለእያንዳንዱ ፍልሚያ ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል።  

         የሁለቱ ቡድኖች የከዚህ ቀደም ግንኙነት 

በላሊጋው ታሪክ ማድሪዶች ከየትኛው ቡድን ጋር ካደረጉት ጨዋታ ብዙ ድል ያገኙት በአትሌቲኮ ማድሪድ ላይ ሲሆን ካለፉት 161 ግንኙነታቸው 86 ያህሉን ድል ነስተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከሜዳቸው ውጪ አትሌቲኮን ድል ያደረጉበት 34 ጨዋታ በየትኛው የላሊጋው ቡድን ላይ ካስመዘገቡት ብልጫ ያለው ነው።

        የሁለቱ ቡድኖች የቅርብ ጊዜ የላሊጋው አቋም

አትሌቲኮ ማደሪድ :  ድአአድአድ 

ሪያል ማድሪድ : ድድድድሽድ 

                የሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ አሰላለፍ

አትሌቲኮ ማድሪድ : ኦብላክ፣ ጁአፍራን፣ ሳቪች፣ ጎዲን፣ ፊሊፔ ሊውዝ፣ ኮኬ፣ ጋቢ፣ ፓርቴይ፣ ሳኡል፣ ግሪዝማን፣ ኮሪአ 

ሪያል ማድሪድ : ካሲላ፣ ካርቫሀል፣ ራሞስ፣ ቫራኒ፣ ማርሴሎ፣ ሞድሪች፣ ካዝሚሮ፣ ክሎዝ፣ ኢስኮ፣ ቤንዜማ፣ ሮናልዶ 

ጨዋታው የሚደረግበት ሰአት :  ምሽት 4:45

ተጠባቂ ውጤት : አትሌቲኮ ማድሪድ 1-0 ሪያል ማድሪድ

Advertisements