የኬኒያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለ ብሔራዊ ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩ አሳወቀ


በ ዕዮብ ዳዲ

ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከዋሊያዎቹ ጋር የተደለደሉት “ሀራምቤ ስታርስ”የሚባሉት የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን ቤልጄማዊውን አሰልጣኝ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርገው መሾማቸውን ይፋ አድርገዋል።

ካፍ በዝግጅት ማነስ ምክንያት የ2018 የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮንስ ሺፕ[ቻን] የአዘጋጅነት እድሉን የነጠቃት ኬኒያ ደካማ እና ትኩረት የማይስበውን የምስራቅና የመካከለኛ ሀገራት [የሴካፋ] ውድድርን በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ላይ ታዘጋጃለች።

ከዚህ ውድድር መጀመር ቀደም ብላም ቤልጄማዊውን ፖል ፑትን ለሁለት አመት የዋና ብሔራዊ ቡድኗ አዲሱ አሰልጣኝ አድርጋ መሾሟን አሳውቃለች።

በሞንባሳ አምስተኛው ጠቅላላ ጉባኤውን እያደረገ የሚገኘው የኬኒያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ አሰልጣኙን በይፋ አስተዋውቋል።

ፓል ፑት

አሰልጣኙ ለሀራምቤ ስታርሶቹ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ የምስራቅ አፍሪካ ቡድንን ለማሰልጠን 150% ዝግጁ መሆናቸው እና ቡድኑን ለማሳደግ የቻሉትን ያህል እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

“እዚህ በመገኘቴ ኩራት እና ደስታ ይሰማኛል።አፍሪካ ውስጥ ላለፉት 12 አመታት በመቆየት አስደሳች ትዝታን አሳልፊያለው።አሁን ደግሞ ከኬኒያ ጋር ሌላ ታሪክ ለመጻፍ ተዘጋጅቻለው።

“እኔ አሰልጣኝ ብሆንም ብቻዬን ስራውን መስራት አልችልም ስለዚህ የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት፣ደጋፊው እና ሚዲያው አጠገቤ እንዲሆኑ እፈልጋለው” በማለት ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

የቀድሞ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ስታንሌ አኩምቢ ደግሞ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ለፖል ፑት ድጋፍ እየሰጡ ስራቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል።

አኩምቢ ብሔራዊ ቡድኑን ይዘው በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ጨምሮ ደካማ ሪከርድ በማስመዝገባቸው ወርደው ረዳት አሰልጣኝ ሆነው እንዲሰሩ ተወስኗል።

የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኒክ ምዌንዳ በበኩላቸው “ዛሬ ትልቅ ነገር አስተዋውቀናል።የብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኞችን አባላት እንዴት ማጠናከር እንዳለብን ስንወያይ ቆይተናል።

“ስለዚህ ቤልጄማዊው ፖል ፑትን አዲሱ አሰልጣኝ አድርገን ቀጥረናቸዋል።እሱ እኛ ያገኘነው ምርጡ ሰው ነው።ለ 2019 የአፍሪካ ዋንጫም ማሳካት እንደሚችል አሁንም እምነቱ አለን።”ሲሉ ተናግረዋል።

ፖል 2012 ላይ የቡርኪናፋሶ አሰልጣኝ ሆነው ከመሾማቸው አስቀድሞ ከ 2008 እስከ 2011 ድረስ የጋምቢያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል። 

በየካቲት 2015 ላይም ከቡርኪናፋሶ ሀላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ በዛው አመት ሰኔ ወር ላይ የጆርዳን ብሔራዊ ቡድንን እንዲያሰለጥኑ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው ሲሰሩ ቆይተዋል።

2016 እና 2017 ላይ ጊኒ እና የዩጋንዳን ለማሰልጠን ከቀረቡት እጩዎች ውስጥ መካተት ችለው ነበር።ከጥቅምት 2016 ጀምሮ ደግሞ ወደ ሰሜን አፍሪካ በማቅናት የአልጄሪያውን ዩኤስ ኤም አልጀርስን ማሰልጠን ችለዋል።

ፖል ፑት እና ኒኪ ምዌንዳ

የ 61 አመቱ ፑት አፍሪካ ውስጥ እንደ ስኬት የሚታይላቸው በ 2013 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ቡርኪናፋሶን ይዘው እስከ ፍጻሜው በመድረስ በናይጄሪያ ተሸንፈው ሁለተኛ ሆነው ማጠናቀቅ የቻሉበት ነው።

ነገርግን የእግርኳስ ህይታቸው ላይ ጥላሸት የቀባው በቤልጄም በጨዋታ ውጤት ማጭበርበር ተከሰው ለሶስት አመታት የተቀጡበት አጋጣሚ እስካሁን ድረስ ስማቸው በመጥፎ መልኩ ያነሳ ሆኗል።

Advertisements