የ 2018 የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንስ ሺፕ[ቻን] ውድድር የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ተካሄደ

በ ዕዮብ ዳዲ


የ2018 በሀገር ውስጥ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ብቻ የሚወዳደሩበት 16 ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮንስሺፕ[ቻን]ውድድር የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት በሞሮኮ ራባት ሶፊትል ሆቴል ይፋ ሆኗል።

በኬኒያ አዘጋጅነት እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረው የ2018 የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮንስ ሺፕ [ቻን] በዝግጅት ማነስ ምክንያት የአዘጋጅነቱን እድሉ ከኬኒያ ተነስቶ ለሞሮኮ እንደተሰጠ ይታወቃል።

ኬኒያን ተክታም ግብፅ በውድድሩ ላይ እንድትሳተፍ ጥሪ ቢቀርብላትም በሀገሯ የሚደረገው የውስጥ ሊግ ላይ ትኩረት በማድረግ በውድድሩ ላይ እንደማትሳታፍ አሳውቃለች።

ካፍ በቀጣይነት እድሉን ለምስራቅ አፍሪካ በመስጠት ከኢትዮጵያ እና ከሩዋንዳ አሸናፊ እንዲሳተፉ ባደረገው መሰረት ሩዋንዳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በደርሶ መልስ ጨዋታ 3-2 በማሸነፍ ያገኘውን እድል መጠቀሙ ይታወሳል።

በተለይ በ አ/አ ስታድየም የተደረገው ጨዋታ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን የዋሊያዎቹን ድክመት ተጠቅም አሸንፎ መሄዶ ወደ ሞሮኮ እንዲያቀና መንገዱን ያመቻቸበት ነበር።

በዚህም መሰረት ለውድድሩ ያለፉት 16 ሀገራት የምድብ ድልድል አርብ ምሽት በሞሮኮ ራባት ሶፊትል ሆቴል ወጥቷል።በዚህም መሰረት


ምድብ አንድ:

ሞሮኮ፣ጊኒ፣ሱዳን፣ሞሪታኒያ

ምድብ ሁለት: 

አይቮሪኮስት፣ዛምቢያ፣ዩጋንዳ፣ናሚቢያ

ምድብ ሶስት:

ሊቢያ፣ናይጄሪያ፣ሩዋንዳ፣ኢኳ.ጊኒ

ምድብ አራት

አንጎላ፣ካሜሮን፣ኮንጎ፣ቡርኪናፋሶ ሆነው ተደልድለዋል።


የምስራቅ አፍሪካዎቹ ዩጋንዳ፣ ሱዳን እና ሩዋንዳ ከ አንድ እስከ ሶስት ባሉት ምድቦች የተደለደሉ ሲሆን በአንጻራዊ ዩጋንዳ የምትገኝበት ምድብ ሶስት ጠንካራ ጨዋታ እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ምድብ አራት ደግሞ ከሌሎቹ ምድቦች በተሻለ ተቀራራቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች የተደለደሉበት በመሆኑ ሊያልፍ የሚችለው አገር  ማን ሊሆን እንደሚችል አጓጊ ሆኗል።

በተለይ የውስጥ ሊጋቸው ጠንካራ የሆነ እንዲሁም ብዙ ጠንካራ ተጫዋቾቻቸው በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ያላቸው ሀገሮች ውጤታማ የመሆን እድላቸው የሰፋ ነው።

ነገርግን አሁንም ቢሆን ውድድሩ በብዙ ሀገራት ትኩረት እየተሰጠው ባለመሆኑ ምናልባትም ተሳታፊ ሀገራት በውድድሩ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሊያስመለክቱን እንደሚችሉ ይጠበቃል።

አዘጋጇ ሞሮኮ ለውድድሩ አራት ስታድየሞችን በተለያዩ ከተሞች[ካዛብላንካ፣ማራካሽ፣ታንገር እና አጋዲር] በማዘጋጀቷ ውድድሩን በስኬት እንደምታጠናቅቅ ይጠበቃል።

በተለይም ዘንድሮ ሞሮኮ በዋና ብሔራዊ ቡድኗ ከረጅም አመት በኋላ ወደ አለም ዋንጫ መመለሷ እንዲሁም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ይሳተፍ የነበረው ዊዳድ ካዛብላንካ አል አህሊን አሸንፎ የ2017 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በማሸነፉ በእግርኳሱ የተነቃቃችበት ወቅት መሆኑ አጋጣሚውን ጥሩ አድርጎታል።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድኗም የዚሁ የመነቃቃት አንድ አካል በመሆኑ ዋንጫውን በሀገሩ በማስቀረት 2017 በልዩነት “የሞሮኮ የስኬት አመት” ለማድረግ  አስበዋል።

ውድድሩ ከሁለት ወራት በኋላ የሚጀመር ሲሆን በፈረንጆቹ ከጥር 13 እስከ የካቲት 4 ድረስ የሚቆይ ይሆናል።የመክፈቻ ጨዋታውንም አዘጋጇ ሞሮኮ ከ ሞሪታኒያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ይጀመራል።


Advertisements