አልማዝ አያና የደልሂ ግማሽ ማራቶንን አሸነፈች

ከአየር ንብረት መዛባት ጋር በተያያዘ ስሙ ሲነሳ የነበረው የደልሂ ግማሽ ማራቶን ውድድር ዛሬ የተካሄደ ሲሆን የመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎዋን ያደረገችው አልማዝ አያና ማሸነፍ ችላለች፡፡

በወንድም ሆነ በሴቶቹ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንፀባራቂ ድል ባስመዘገቡበት የደልሂ ግማሽ ማራቶን አልማዝ አያና የሴቶቹን ዘርፍ 1:07:11 በሆነ ሰዓት በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ስትችል ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አባበል የሻነ እና ነፃነት ጉደታ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

በወንዶቹ ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያዊው ብርሃኑ ለገሰ 59:46 በሆነ ሰዓት ድል ያደረገ ሲሆን ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አንዳምላክ በልሁ ብርሃኑን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ አሜሪካዊው ሊዮናርዶ ኮሪር በሶስተኝነት ውድድሩን ያጠናቀቀ አትሌት ሆኗል፡፡

ውድድሩን ላሸነፉት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ 27 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደተሰጠ የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡

Advertisements