ቁጥሮች ይናገራሉ / ትኩረት የተነፈገው ነገርግን አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው ቶትነሀም ከስድስት የሊጉ ሀያላን ቡድኖች ጋር ያለው ደካማ የውጤት ሪከርድ

ቅዳሜ አመሻሽ በነበረው የሰሜን ለንደን ደርቢ ከዚህ ቀደም በአርሰናል ቤት እንደ አድሎኛ ይታዩ የነበሩት ማይክ ዲን በመድፈኞቹ በተሞገሱበት ጨዋታ የአርሰናል ግቦች በተቆጠሩበት ወቅት ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖን በስፐርሶች ላይ ማሳደራቸው እና ከጉዳት የተመለሱት ሀሪ ኬንን የመሰሉ ኮከቦች ተገቢ የጨዋታ ብቁነት ላይ አለመድረሳቸው ለሽንፈቱ በፖቸቲኖ እንደ ምክንያት ቢነሳም ቀጣዩ የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለ ዘገባ ግን በተቃራኒው ቶትነሀም በሊጉ ትክክለኛ የዋንጫ ተፋላሚ ለመሆን መቅረፍ ያለበት አንድ ከባድ ችግር እንዳለ ከቅዳሜው ፍልሚያ ጋር አስተሳስሮ እንደሚከተለው ቁጥሮችንና እውነታዎችን እየጠቀሰ በዝርዝር ይነግረናል።


ምንም እንኳን ቶትነሀም ቤት ነገሮች አዎንታዊ መስለው እየተጓዙ ወደአዲስ ስታዲየም የሚደረገው ሽግግር እየቀረበና ስብስቡ በተሰጥኦ በተሞሉ ታዳጊዎች የተሞላ ቢሆንም የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከሜዳው ውጪ ከትልልቆቹ ስድስቱ ጋር ያለው የእርስበርስ ግንኙነት ሪከርድ እጅግ አሳሳቢ ነው። 

የማውሪሲዮ ፖቸቲኖው ቶትነሀም ከማንችስተር ዩናይትድ፣ አርሰናል እና ሊቨርፑል ጋር ባደረገው የመጨረሻ 87 ከሜዳው ውጪ ጨዋታ ማሸነፍ የቻለው አራቱን ብቻ ነው። አርጀንቲናዊው የክለቡ አለቃ ምንም እንኳን ስብስባቸው በሊግ ጨዋታ በአርሰናል ሲረታ የቅዳሜው የመጀመሪያ ጊዜያቸው ቢሆንም ከትልልቆቹ ስድስቱ ጋር በነበራቸው ከሜዳ ውጪ ትንቅንቅ ያስመዘገቡት ድል አንድ ብቻ ነው።  

በቅዳሜው ጨዋታ ከጉዳት መልስ የሀሪ ኬን እና ሙሳ ዴምቤሌ ለጨዋታው በሚገባው መልኩ ብቁ ሆኖ አለመመለስ እንዲሁም የዕለቱ የጨዋታ ዳኛ ማይክ ዲን በሁለቱም የአርሰናል ግቦች ላይ የነበራቸው ተፅዕኖ በቶትነሀም ላይ እንዳንፈርድበት ቢያደርገንም ቶትነሀም ሁሌም ከትልልቆቹ ጋር ያለው ደካማ ሪከርድ በክለቡ ላይ ሀዘኔታ እንዳይኖረን ያደርገናል። 

ፖቸቲኖ ለዚህ የቡድናቸው ችግር መከላከልን እንደ ምክንያት ያቀርባሉ። ነገርግን ትልልቆቹ ስድስቱ ቡድኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ከሜዳቸው ውጪ እርስበርስ ሲገናኙ እንደ ቶትነሀም ሁሉ ትልቅ የመከላከል ችግር የሚያሳዩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ባሳለፍነው ቅዳሜ የነበረው ጨዋታ ውጤት በዋነኛነት የተወሰነው አርሰናል ከሚታማበት በተቃራኒው በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ባሳየው አስደናቂ እግር ኳስና የሜዳ ላይ ዲሲፕሊን ነበር። 

ከዛም የቅዳሜው ትንቅንቅ ወደ 2-0 በተቀየረበት ወቅት ቶትነሀም አጥቅቶ ለመጫወት ጥረት ማድረጉ አስደማሚ ፍጥነታቸው ምንም መቀነስ ባላሳየው አሌክሲ ሳንቼዝ እና አሌክሳንደር ላካዜቲ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥቃት እንዲደርስበት ምክንያት ሆኗል። ፖቸቲኖ በዳኛ ስህተቶች ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውም በአብዛኛው በአርሰናል ተጭኖ የመጫወት መንገድ የተከሰተውን የቡድናቸውን የመከላከል ስህተት ያስረሳቸው ይመስላል። 

በዕለቱ የቶትነሀምን ችግር በዴምቤሌና ሙሳ ሴሴኮ የአማካኝ ጥምረት የመጣ መሆኑን እና ሁለቱ ተጫዋቾች ከአካል ብቃታቸው መፈርጠም ውጪ ጨዋታውን መቆጣጠር አለመቻላቸው ተነስቶ ትችት ዘንቦባቸዋል። የስፐርስን የዕለቱን ሁለት አማካኞች ጥምረትም ከእንቅስቃሴ እስከ ጭንቅላት ድረስ የተጣረሰና መሆኑን እና ሁለቱ አማካኞች ከተቃራኒዎቻቸው የሚደርስባቸውን ግፊት መቋቋም አለመቻላቸው በትልቁ ተወስቶላቸዋል።

ከሁለቱ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ደግሞ ሲሶኮ ትልቅ ጫና ያለባቸውን የደርቢ ጨዋታ የመቋቋም ችግር ያለበት ተጫዋች መሆኑን ተደብቀው የቆዩት ቁጥሮች ይፋ አድርገዋል። ሲሶኮ ቅዳሜ አመሻሽ በነበረው ፍልሚያ ቡድኑ ከአርሰናል ጋር ባደረገው የደርቢ ትንቅንቅ በቋሚ ተሰላፊነት የጀመረው የመጀመሪያ ጨዋታው መሆኑ ቢታወቅም ከዚህ ቀደም በኒውካስትል ከሰንደርላንድ ጋር በነበረው ጨዋታ ለሰባት ጊዜያት እንዲሁም በቱሉዝ ቆይታው ከቦርዶክስ በነበረው ተመሳሳይ ሰባት የደርቢ ፍልሚያ በቋሚነት ከጀመራቸው አጠቃላይ 14 የደርቢ ጨዋታዎች አንድ ድል፣ አንድ የአቻ ውጤት ሲኖረው በ 12ቱ ሽንፈትን መከናነቡ ገሀድ ወጥቶለታል።

በዕለቱ ከቦታ አያያዝ አንፃር በቁጥር ለማስቀመጥ ቢቸግርም በሸርተቴም ሆነ ኳስ በማጨናገፍ ረገድ በጨዋታው ላይ ሲሶኮ ከአማካኝ ተከላካይ ከሚጠበቀው በተቃራኒው ከተቃራኒ ተጫዋቾች ኳስ መቀማት የቻለው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሲሆን አርሰናል በአብዛኛው ስህተት በሰራበት ከቶትነሀም ኋላ ክፍሉ ፊት ባለው ቦታ ላይ ለነበረው የስፐርስ ችግርም ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል በሚል የጨዋታው ትልቁ ውድቀት ተደርጎ ስሙ በተደጋጋሚ ተነስቷል።  

በአጠቃላይ ግን በቅዳሜው ጨዋታ ቶትነሀም የውሳኔዎች መዛባትና ከጉዳት መልስ የወሳኝ ተጫዋቾች ለጨዋታ ብቁ የመሆን ችግር የፓቸቲኖን ንግግር ትክክለኛነት በሚያሳይ መልኩ በወጣቶች ለተሞላው ስብስብ ሽንፈት እንደ ተገቢ ምክንያት ሊነሳ ቢችልም ጉዳዩን አስፍተን ስንመለከተው የስፐርስ ከሜዳ ውጪ ሪከርድ እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በሊጉ ከትልልቆቹ ስድስቱ ገና ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ያሉት የፖቸቲኖ ስብስብ እውነተኛ ተፎካካሪ መሆኑን ለመለየት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከሲቲ የሚያደርገው ጨዋታ ትልቅ መነሻ ፍንጭ እንደሚሆን እሙን ነው።

Advertisements