ኢብራሂሞቪች ጉዳቱ ሰዎች ከሚያውቁት በላይ እንደሆነ ገለፀ

የማንችስተር ዩናትዱ ኮከብ ዝላታን ኢብራሂሞቪች የጉልበት ጉዳቱ ከዚህ ቀደም ከሚታወቀውም በላይ የከፋ እንደሆነ ገለፅዋል።

ስዊድናዊው አጥቂ ማንችስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ኒውካሰልን 4ለ1 በሆነ ውጤት በረታበት ጨዋታ ከተቀያሪ ወንበር ላይ በመነሳት ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታ ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል።

የ36 ዓመቱ ኢብራሂሞቪች ምንም እንኳ የጉዳቱን ክብደት በሚስጥር ይዞ መቆየትን ቢመርጥም ጉዳቱ ከዚህ ቀደም ከሚታወቀውም በላይ የከፋ እንደሆነ ግን ተናግሯል።

“ሰዎች እውነተኛውን ጉዳት ቢያውቁ እስካሁን መጫወት መቻሌ እንኳ ድንጋጤ ውስጥ ይከታቸዋል። ከጉልበትም በላይ ነበር። ነገር ግን [በሚስጥር] ለራሴ አቆየዋለሁ። ለዚህም ነው ሰለዚያ ማውራትን ያልመረጥኩት።” ሲል ለእንግሊዝ ጋዜጦች ተናግሯል።

“በማገገሚያዬ ወቅት በምንም ነገር ላይ አልተጣደፍኩም። ለስድስት ወር ከግማሽ [ከጨዋታ] ውጭ ሆኛለሁ። የሚሰጠኝን መመሪያ እና የድርጊት መርሃግብሬን በየዕለቱ ስከታተል ቆይቻለሁ።

“ብቸኛው ሚስጥር ጠንክሬ ስሰራ መቆየቴ ነው። ምን ሳደርግ እንደነበር ከእኔ ጋር ቅርበት ያላቸው ያውቁታል። በየዕለቱ ለአምስትና ለስድስት ሰዓታት ስስራ ቆይቻለሁ።” ብሏል።

ኢብራሂሞቪች ባለፈው የውድድር ዘመን ለክለቡ የፈረመው የአንድ ዓመት ኮንትራቱ እስከተጠናቀቀባት ጊዜ ድረስ ለማንችስተር ዩናይትድ በሁሉም ውድድሮች ላይ 28 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

አንጋፋው ተጫዋች ኮንትራቱ አሁን ሊጠናቀቅ የተቃረበ ሊሆን ቢችልም፣ ነገር ግን ተጫዋቹ የወደፊት ዕጣ ፈንታው አላስጨነቀውም።

“በአሁኑ ጊዜ ዳግም መሮጥ፣ መግፋትና እግርኳስ መጫወት በመቻሌ አመሰግናለሁ።” ሲል ኢብራሂሞቪች ተናግሮ “መጪው ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ አላውቅም። ነገር ግን የሆነው ነገር ሆኗል። ምን ማድረግ እንደምፈልግ የምመርጥበት ዕድሜ ላይ እገኛለሁ።

“የአምስት ወይም የ10 ዓመት ስምምነት አላደርግም። ወደጨዋታ መመለሴና ጥሩ የሆንኩበትን ነገር በማድረጌ ደስተኛ ነኝ።

“መጫወት የሚያስደስት ነገር ነው። ጆዜም ‘ማድረግ የምትፈልገውን ነገር አድርግ። ባንተ እምነት አኝ። አንተ ደግሞ የምታደርገውን ነገር ታውቃለህ።’ ብሎኛል። ስለዚህ አልተጨነቅኩም።

“ኮንትራቱ የወረቀት ጉዳይ ብቻ ነው። የተግባር ስራውን ግን እኔ አተገብረዋለሁ።” ሲል ተጫዋቹ ሃሳቡን ገልፅዋል።

Advertisements