ምርመራ / ሊቨርፑል ከትናንት ምሽቱ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ጋር በተያያዘ የደጋፊዎቹን ቅሬታ እያጣራ እንደሆነ አስታወቀ


በሚኪያስ በቀለ

ሊቨርፑል ትናንት ምሽት ከሲቪላ ጋር በነበረው የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ደጋፊዎቹ በስፔን ፖሊስ ያልተገባ አያያዝ፣ ትንኮሳ እና ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ የመከልከል ድርጊት እንደተፈፀመባቸው የቀረበውን ቅሬታ እያጣራ መሆኑን አስታውቋል። 

ቀያዮቹ  ከመምራት ተነስተው በ 3-3 አቻ ውጤት በፈፀሙት የምሽቱ የምድብ ትንቅንቅ ፍልሚያ ጨዋታው በሚጀመርበት ወቅት የእንግዳው ክለብ ደጋፊዎች መቀመጫ ግማሽ ያህል ባዳ ሆኖ ታይቷል። 

ለዚህ ችግር መፈጠርም ምክንያቱ በር ላይ የተፈጠረ መንጓተት እና የሊቨርፑል ደጋፊዎች መጀመሪያ ከተመደቡበት ወንበር በተቃራኒ በተገኘው ቦታ ገብተው እንዲቀመጡ ወይም እንዲሄዱ መገደዳቸው መሆኑ በቅሬታ መልክ ተወስቷል። 

ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ማረጋገጫ ባይገኝም የእንግሊዙ ክለብ ደጋፊዎች በማህበራዊ ሚዲያ የለቀቋቸው ፅሁፎች በስፔን ፖሊስ ጥቃት እንደደረሰባቸው ጭምር የሚገልፁ ሆነው ታይተዋል። 

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም የአንፊልዱ ክለብ በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫ የትናንት ምሽቱን ጨዋታ ለመከታተል የሄዱ ደጋፊዎቹን በተመለከተ የስታዲየሙ አስተናባሪዎችና የአካባቢው ፖሊሶች የነበራቸውን አያያዝ እንደሚያጣራ ገልጿል።  

የአምስት ጊዜው የውድድሩ አሸናፊው ሊቨርፑል በመግለጫው የክለቡ ደጋፊዎች ጥበቃና ሰላም ሁሌም ተቀዳሚ ትኩረቱ መሆኑን እና ተጨማሪ መረጃዎችን ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ እንደሚለቅ ጨምሮ አስታውቋል።

Advertisements