ውዝግብ / ሮናልዶ ለዘንድሮው የማድሪድ የውጤት ቀውስ መፍትሔው የቡድኑን አንድ ተጫዋች ማሰናበት መሆኑን ለፍሎረንቲኖ ፔሬዝ መናገሩ ይፋ ሆነ


በሚኪያስ በቀለ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ የቡድን አጋሩ ኢስኮ “የተበላሸ አፕል” መሆኑንና ለቡድኑ ህልውና ሲባልም ስፔናዊው ኮከብ ከቡድኑ መቀነስ እንዳለበት ለክለቡ ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ መናገሩ ተገለፀ።

ሪያል ማድሪድ ትናንት ምሽት በቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ አፖል ኒኮሲያን በግማሽ ደርዘን ግብ ሲረታ ሮናልዶ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ የግብ ድርቀቱን ሲፈታ ካሪም ቤንዜማ በተመሳሳይ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የስፔኑ ክለብ የውድድር ዘመኑን በደካማ ውጤት ውስጥ ሆኖ እየተጓዘ ባለበትና በላሊጋው ገና ካሁኑ ከተቀናቃኙ ባርሴሎና በ 10 ነጥቦች በራቀበት ሰአት ሮናልዶ ለቡድኑ ችግር መፍትሄ የሚለውን ሀሳብ ለክለቡ ፕሬዝዳንት ማቅረቡ ተነግሯል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የእንግሊዙ ዴይሊ ኤክስፕረስ የስፔኑን ሳምንታዊ የስፖርት መፅሄት ዶን ባሎንን ጠቅሶ እንደፃፈው ሮናልዶ እሱና ቤንዜማ ኢስኮ በሌለበት የተሻለ መንቀሳቀስ እንደሚችሉና አሴንሲዮም በእሱ (በኢስኮ) ቦታ ተተክቶ እንዲሰለፍ ፍላጎቱን መግለፁ ታውቋል። 

ከዚህ በተጨማሪም አሴንሲዮ ተቀያሪ ወንበር ላይ የሚቀመጥ ከሆነ ሮናልዶ ከቡድኑ እንዲቀነስ በሚፈለገው ኢስኮ ቦታ ቤል ተክቶት እንዲጫወት መፈለጉን ለክለቡ ፕሬዝዳንት ማስታወቁ ተያይዞ ተገልጿል።

ኢስኮ ባሳለፍነው አመት መጨረሻ አስደናቂ ብቃት በማሳየት ዚነዲን ዚዳንን አሳምኖ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ባነሱበት ወቅት ትልቅ ሚናን መወጣቱ አይረሳም። 

የቀድሞው የማላጋ ኮከብ በአዲሱ የውድድር ዘመን በላሊጋው 12 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሮናልዶና ቤንዜማ በጋራ ማስቆጠር የቻሉት ሁለት ግቦችን ብቻ ነው። 

የዚዳን ስብስብ የሊግ አቋም ፔሬዝን ባሳሰባቸው በዚህ ሰአት ሮናልዶ ለክለቡ ችግር መፍትሄው የቡድኑን የወቅቱን ወሳኝ ተጫዋች ኢስኮን መቀነስ መሆኑን ለክለቡ ፕሬዝዳንት መግለፁ  የሚኖረው እንድምታ በጉጉት ይጠበቃል።

Advertisements