የረቡዕ ምሽት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ቁልፍ ቁጥራዊ መረጃዎች

ባርሴሎና ዛሬ ምሽት በሚያደርገው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የምድቡን መሪነት አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስቸለው አዎንታዊ ነጥብ የማግኘት ዕቅድ ይዞ ጁቬንቱስን ይገጥማል።

ሊዮኔል መሲም በሻምፒዮንስ ሊጉ ላይ አዲስ የግሉን የክብረወሰን መሰረት ለመጣል ተቃርቧል። በአንፃሩ በኑ ካምፕ የ3ለ0 ሽንፈት የገጠመው ጁቬንቱስም የ16 ቡድኖችን ለመቀላቀል የሚችልበትን ውጤት ለማግኘት ይፋለማል።

በሌላ በኩል ማንችስተር ዩናይትድ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያውን ለመቀላቀል ከጫፍ ይገኛል። ከጉዳት የተመለሰው ፖግባም በውድድሩ ላይ ያለውን መጥፎ የሚባል ቁጥራዊ መረጃ ለማሻሻል ይጫወታል። እንዲሁ የፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂም ከብሬንዳን ሮጀርሱ ሴልቲክ እጅ ነጥብ የመፈልቀቅ ኃላፊነት ከፊቱ ተደቅኗል።

ቼልሲም ከካራባግ ጋር በሚያደርገው የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ሃዛርድ ወቅታዊን ድንቅ ብቃቱን ለማስቀጠል የሚጫወት ሲሆን፣ በዚሁ ምድብ አትሌቲኮ ማድሪድ በስፔኗ መዲና ከምድቡ መሪ ሮማ ጋር ወሳኝ የሞት ሽረት ፍልሚያ ያደርጋል። 

ተከታዩ ፅሁፍም የስፖርት ቁጥራዊ መረጃዎችን እየመዘገበ የሚተነትነው ኦፕታ ያሰፈራቸውን ከረቡዕ ምሽቱ ጨዋታዎች ጀርባ ያሉትን ቁልፍ ቁጥራዊ መረጃዎችን ያስቃኘናል።

ሲኤስኬኤ ሞስኮ ከ ቤኔፊካ

57 – ሲኤስኬኤ በመጀመሪያው አራት ጨዋታዎቹ ስድስት ነጥቦችን ሰብስቧል። ከ2003-04 ወዲህም ወደቀጣዩ የማጣሪያ ዙር ለማለፍ 57 ከመቶ የማለፍ ዕድል ሲይዝ ይህ የመጀመሪያው ነው።

5 – ቤኔፊካ ለመጨረሻ ጊዜ በተከታታይ ያደረጋቸውን አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፏል። በዚህ ሂደትምም ማስቆጠር የቻለው አንድ ግብ ብቻ ነው። ከቤኔፊካ ያነስ የግብ ቁጥር (0) ያለውም አንደርሌክት ብቻ ነው። 

ባሰል ከ ማንችስተር ዩናይትድ

13 – በአውሮፓ ውድድሮች ላይ ከባስል ጋር በተደረገ ጨዋታ (13 ጨዋታዎች) ግብ ያልተቆጠረበት የእንግሊዝ ክለብ የለም። የስዊዘርላንዱ ክለብ ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር በሜዳው ካደረጋቸው ያለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን 1ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

33 – ፖል ፖግባ በ33 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ማስቆጠር የቻለው ሁለት ግቦችን ብቻ ነው።

ፒኤስጂ ከ ሴልቲክ

17 – ፒኤስጂ በሻምፒዮንስ ሊጉ በዚህ የውድድር ዘመን ከየትኛውም ቡድን በላይ ብዙ ግቦችን (17) ማስቆጠር ችሏል። እንዲሁም በውድድሩ ላይ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ መረቡን በዝቅተኛ ቁጥር ያላስደፈረው ፒኤስጂ ብቻ ነው።

2 – ብሬንዳን ሮጀርስ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በሻምፒዮንስ ሊጉ ላይ ካደረጓቸው 16 የምድብ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት ሁለቱን ብቻ ነው። እነዚህም በ2014 በሊቨርፑል የአሰልጠኝነት ዘመናቸው ሉዶጎሬትስን 2ለ1 ያሸነፉበትና ሴልቲክ አንደርሌክትን 3ለ0 መርታት የቻለባቸው ጨዋታዎች ናቸው።

አንደርሌክት ከ ባየር ሙኒክ 

18 – አንደርሌክት ባለፉት 18 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎቹ ግብ ያልተቆጠረበት በአንዱ ጨዋታው ላይ ብቻ ነው። 

29 – ባየር ሙኒክ ከአንደርሌክትን 3ለ0 በረታበት የመጀመሪያው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ወደግብ ካደረጋቸው 29 ሙከራዎች 11 ያህሉ ዒላማቸውን የጠበቁ ነበሩ። በእንፃሩ አንደርሌክት ያደረገው ደግሞ አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ነበር።

ካራባግ ከ ቼልሲ

90 – ካራባግ በሻምፒዮንስ ሊጉ በዚህ የውድድር ዘመን አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። ከ2003-04 ወዲህም በሶስት አጋጣሚዎቹ ላይ ብቻ 16 ውስጥ መግባት ችሏል። በእነዚህም 90 በመቶ ጨዋታዎች ላይ በመጀመሪያ አራት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ደርሶበታል። 

17 – ኤዲን ሃዛርድ በ2017-18 የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ከየትኛውም ተጫዋች በላይ የግብ ማስቆጠር ዕድሎችን (17) መፍጠር ችሏል።

አትሌቲኮ ማድሪድ ከ ሮማ

4 – ሮማ ከስፔን ክለቦች ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ሽንፈት ገጥሞታል። (አንዱን ደግሞ አሸንፏል)፣ በእነዚህ ጨዋታዎች ላይም 15 ግቦች ተቆጥረውበታል (በአማካኝ በየጨዋታው ሶስት ግቦች ማለት ነው።)

9 – አትሌቲኮ ማድሪድ ካለፉት 14 የመጨረሻ የሻምፒዮንስ ሊግ ግቦቹ ዘጠኙ የአንትዋን ግሪዝማን ቀጥተኛ ተሳትፎ አለባቸው (ሰባቱን ሲያስቆጥር፣ ሁለቱን ዳግሞ አመቻችቶ አቀብሏል።)

ስፖርቲንግ ከ ኦሎምፒያኮስ

1 – በዚህ የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊጉ ከኦሎምፒየኮስ (ዘጠኝ ሙከራዎች) ያነሰ ዒለማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገው ብቸኛ ክለብ ካራባግ ነው።

19 – የኦሎምፒያኮሱ ግብ ጠባቂ ሲልቪዮ ፕሮቶ በዚህ የውድድር ዘመን ተሰልፎ በተጫወተባቸው ሶስት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች 19 የግብ ሙከራዎችን ማዳን ችሏል። ይህ ዳግሞ በዚህ የውድድር ዘመን ከየትኛውም የግብ ጠባቂ የሚበልጥ ነው።

ጁቬንቱስ ከ ባርሴሎና

29 – ጁቬንቱስ ከስፔን ክለቦች ጋር በሜዳው ባደረጋቸው ያለፉት 29 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች የተሸነፈው በአንዱ ብቻ ነው (ድል 19፣ አቻ 9)። ከእነዚህ ጨዋታዎችም በመጨረሻ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች የተቆጠረበት ግብ አንድ ብቻ ነው። 

100 – ሊዮኔል መሲ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ቀጥሎ በሻምፒዮንስ ሊጉ 100 ግቦችን ያስቆጠረ ሁለተኛ ተጫዋች ለመሆን አንድ ሃትሪክ መስራት ብቻ ይቀረዋል።

Advertisements