ቁጥሮች ይናገራሉ / በመላው አውሮፓ ብዙ ደቂቃዎችን ለክለቦቻቸው ተሰልፈው መጫወት የቻሉ 10 ተስፈኛ ታዳጊዎች

በእግር ኳስ አለም አንዱ ትውልድ ሲሸኝ ሌላው መተካቱ አይቀሬ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሮናልዶና ሜሲ እድሜ 30ዎቹን በተሻገረበት በዚህ ሰአት በቀጣይነት እነሱን ተክተው በአውሮፓና በአለም እግር ኳስ የሚደምቁ ታዳጊዎች ብቅ ብቅ ብለዋል። የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለም በቀጣዩ ዘገባው በአህጉረ አውሮፓ ከእድሜያቸው በላቀ ለክለቦቻቸው ብዙ ደቂቃዎችን ተሰልፈው መጫወት የቻሉ 10 ያህል ተስፈኛ ታዳጊዎችን ያስተዋውቀናል። 


በሚኪያስ በቀለ

1. ጂያንሉጂ ዶናሩማ (ኤሲ ሚላን) – 1170 ደቂቃዎች

በእርግጥም ዶናሩማ ጥሩ ተጫዋች ነው። ገና በ 18 አመት እድሜው ላይ የሚገኘው ተጫዋች በዘንድሮው የውድድር ዘመን በእያንዳንዱ ደቂቃ ለኤሲ ሚላን ተሰልፎ መጫወት የቻለ ሲሆን ከጂያንሉጂ ቡፎን ጡረታ መውጣት በኋላም የጣሊያን ቁጥር 1 እንደሚሆን ይጠበቃል። 

2. ክርስቲያን ፑልሲች (ቦሩሲያ ዶርትሙንድ) – 849 ደቂቃዎች

ፑልሲች በቅርቡ “ኳስን መያዝ፣ ይዞም መሮጥ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ማለፍ እወዳለሁ።” ሲል ከእንግሊዙ ጋዜጣ ኢንዲፔንደት ጋር በነበረው ቆይታ መናገሩ ይታወሳል። 

የዶርትሙንዱ ኮከብ ሀገሩ አሜሪካ ለሩሲያው አለም ዋንጫ ባለማለፏ ቁጭት ውስጥ ቢገኝም ለክለቡ ወሳኝ ሚና መጫወቱን እንደቀጠለ ነው።  

3. ዳዮቶቻንቹሌ ኡፓምካኖ (አርቢ ሊፕዚግ) – 832 ደቂቃዎች

አርቢ ሊፕዚግ በቅርብ አመታት ውስጥ በተሰጥዖ በተሞሉ ወጣቶች የተሞላ ስብስብ መናሀሪያ መሆኑ በአድናቆት የሚወራለት ክለብ ሲሆን ኡፓምካኖም አዲሱ የቡድኑ አይን ማረፊያ ኮከብ ነው። 

የፈረንሳዩ መሀል ተከላካይ ባሳለፍነው አመት ጥር ወደ ቡንደስሊጋው ክለብ ባመራበት ወቅትም አርሰናል እና ባርሴሎና ፍላጎት አሳድረውበት እንደነበር አይረሳም።

4. ዴኒስ ጊይጋ (ሆፈንየም) – 751 ደቂቃዎች

ጊይጋ መስከረም ላይ ከሻልክ ጋር በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያውን የቡንደስሊጋ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ጁሊያን ኒግልስማን ታዳጊውን የገለፁት “ለ 19 አመት ተጫዋች እሱ ምርጥ ደምበኛ ነው” በማለት ነበር። 

የሆፈንየም ደጋፊዎች ሰባስቲያን ሩዲና ኒክላስ ሱሌ በክለቡ የሚተካቸው አይኖርም ብለው ቢሰጉም የስሙ ትርጉም “ቫዮሊን ተጫዋች” የሚል ትርጉም ያለው ጊይጋ ሙዚቃው እንደማይቆም ማረጋገጫ እየሰጣቸው ይገኛል።

5. ፌደሪኮ ቫልቬርዴ (ዲፖርቲቮ) – 706 ደቂቃ

የላሊጋው ብቸኛ ተወካይ ቫልቬርዴ ከሪያል ማድሪድ ለቆ በውሰት ዲፖርቲቮ የሚገኝ ሲሆን በ 2015 ለአንድ ሳምንት በአርሰናል ቆይቶ ልምምድ መስራቱም ይታወሳል።

ዲፖርቲቮ በላሊጋውን የደረጃ ሰንጠረዥ መጨረሻ ላይ ተቀምጦ እየተንገታገተ ቢሆንም ቫልቨርዴ ያለው የአንድ አመት የውሰት ውል ቢጠናቀቅም በዛው የመቆየት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። 

6. ቲሞቲ ፎሱ ሜንሳህ (ክሪስታል ፓላስ) – 702 ደቂቃዎች

ክሪስታል ፓላስ አስቸጋሪ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ቢገኝም ከቼልሲና ማንችስተር ዩናይትድ በውሰት ያመጣቸው ታዳጊዎች አስደናቂ ብቃት ማሳየታቸው ለንስሮቹ አዎንታዊ ሂደት ይመስላል። 

በተያያዘ መልኩ ሮበን ሎፍተስ ቺክ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ሰብሮ መግባት ሲችል ፎሱ ሜንሳህ በበኩሉ ለሀገሩ ሆላንድ ሁለት ጨዋታዎችን በማድረግ ተመሳሳይ ስኬት ላይ ይገኛል። 

7. ዳን አክሴል ዛጋዱ (ቦሩሲያ ዶርትሙንድ) – 647 ደቂቃዎች

ቁመተ መለሎው ፈረንሳዊ ሌላኛው የቡንደስሊጋ ተስፈኛ ባለተሰጥኦ ታዳጊ ዛጋዱ ሲሆን ገና 18 አመት እድሜው ላይ ቢገኝም በቦርሲያ ዶርትሙንድ ትልቅ ስኬት እንደሚኖረው ተጠብቋል።

8. ፌደሪኮ ቼይዛ (ፊዮረንቲና) – 626 ደቂቃዎች

በፎርፎርቱ መፅሄት የአመቱ 100 አስደናቂ ታዳጊዎች ምርጫ አራተኛ ደረጃን ያገኘው ቼይዛ በጥቅምት መጨረሻ ገና 20ኛ አመቱን የደፈነ ቢሆንም በፊዮረንቲና ዋናው ቡድን ብቃቱን ማስመስከር ችሏል።  

በ 1999 የያኔው የአውሮፓ ማህበረሰብ (የአሁኑን ኢሮፓ ሊግ) አሸናፊ የፓርማ ስብስብ ተጫዋች የነበረው ኤነሪኪ ቼይዛ ልጅ የሆነው የጣሊያኑ ክለብ ተስፈኛ ይፋዊ ጨዋታ ላይ ባይሆንም ለአዙሪዎቹ ዋና ቡድን ተሰልፎ እስከመጫወት ደርሷል። 

9. ማርከስ ረሽፎርድ (ማንችስተር ዩናይትድ) – 613 ደቂቃዎች

ጆሴ ሞውሪንሆ በወጣት ተጫዋቾች ላይ ብዙም እምነት ያላቸው አሰልጣኝ ባይሆኑም ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከየትኛው የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች በላይ 53 ያህል ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል።

10. ካይ ሀቬርትስ (ባየር ሊቨርኩሰን) – 591 ደቂቃዎች

ሀቬርትስ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ለጀርመኑ ክለብ ሲሰለፍ በሊቨርኩሰን ታሪክ ለዋናው ቡድን በትንሽ እድሜው የተጫወተ ታዳጊ መሆን የቻለ ሲሆን በቻምፒዮንስ ሊጉ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር በነበረው ጨዋታም የትምህርት ፈተና ስለነበረው ጨዋታው እንዳመለጠው አይረሳም። 

የቀድሞው የጀርመን ተጫዋች ሩዲ ቩለር ተስፈኛውን ታዳጊ ከሜሶት ኦዚል ጋር ያነፃፀረው ሲሆን ወደ ሊቨርፑል ሊያመራ የሚችልበት ትልቅ እድል እንዳለም እየተነገረ ይገኛል።

        የፎርፎርቱ የ 2017 የአለም ምርጥ አምስት ታዳጊዎች

1. ጁያንሉጂ ዶናሩማ

2. ክልያን ምባፔ

3. ማርከስ ረሽፎርድ

4. ክርስቲያን ፑልሲች

5. ፌደሬኮ ቼይዛ

የህዳግ ማስታወሻ : የተሟላውን የ 2017 የአለም ምርጥ 100 ታዳጊዎች ዝርዝር በቀጣይ ቀናት ይዘን የምንመለስ ይሆናል።

Advertisements