አስደንጋጭ / ሮቢንሆ የዘጠኝ አመታት የእስር ውሳኔ ተላለፈበት


በሚኪያስ በቀለ

የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ ብራዚላዊ አጥቂ ሮቢንሆ ከአመታት በፊት በጣሊያን በተፈፀመና ተሳትፎበታል በተባለ የወሲብ ጥቃት የዘጠኝ አመታት የእስር ውሳኔ ተላልፎበታል።  

የ 33 አመቱ ተጫዋች ውሳኔው የተላለፈበት በፋሽን ከተማዋ ሚላን ባለ አንድ ጭፈራ ቤት በ 2013 ጥር በአንዲት አልባኒያዊት ሴት ታዳጊ ላይ በተፈፀመ የወሲብ ጥቃት ከተሳተፉ አምስት ሰዎች አንዱ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑ ተገልጿል። 

የወሲብ ጥቃቱ በሚፈፀምበት ወቅት የሚላን ተጫዋች የነበረው ሮቢንሆ ከአመታት በፊት የእንግሊዝን የዝውውር ክብረ ወሰን በመስበር ለማንችስተር ሲቲ መፈረሙ የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ሰአት በሀገሩ ብራዚል በሚገኘው አትሌቲኮ ሚኔሮ እየተጫወተ ይገኛል።  

ለሀገሩ ብራዚል 100 ጨዋታዎችን ያደረገውና በወጣትነት እድሜው ከፔሌ ጋር ይነፃፀር የነበረው ሮቢንሆ ፈፅሞታል ተብሎ የእስር ቅጣት ውሳኔ የተላለፈበትን ወንጀል የካደ ሲሆን በውሳኔው ላይ ይግባኝ የማለት መብት እንዳለውም ታውቋል።  

የጣሊያኑን ጋዜጣ ዴሎ ስፖርትን ጠቅሶ ዘሰን እንደፃፈው ከሆነ ደግሞ ሮቢንሆ በአሁን ሰአት በሀገሩ ብራዚል የሚገኝ በመሆኑ ቅጣቱን ለማስፈፀም ለጣሊያን ተላልፎ በመሰጠቱ ዙሪያ ውሳኔው የደቡብ አሜሪካዋን ሀገር ባለስልጣናት የሚመለከት መሆኑ ተነግሯል።

በሌላ በኩል የእንግሊዙ ታማኝና ተከባሪ ጋዜጣ ዘጋርዲያን ከምንጮቼ አገኘሁት ባለው መረጃ ተመስርቶ እንደፃፈው ከሆነ በጣሊያን ህግ መሰረት ሮቢንሆ ሁለት የይግባኝ መብት የሚኖረው ሲሆን ውሳኔው የሚፀና ከሆነም ቅጣቱን ለማስፈፀም ጣሊያን ሮቢንሆ ተላልፎ እንዲሰጣት የምትጠይቀው የክስ ሂደቱ ሲጠናቀቅ መሆኑ ተገልጿል።

ነገርግን ጋዜጣው ዘገባውን በመቀጠል ብራዚል ዜጎቿን አሳልፋ እንደማትሰጥና ያም ማለት ሮቢንሆ ተይዞ ቅጣቱን እንዲፈፀም ለጣሊያን ሊሰጥ የሚችለው በሌላ ሶስተኛ ሀገር ላይ ከተገኘ እንደሆነ ፅፏል። 

ከዚህ በተጓዳኝ ክሱ እስኪጠናቀቅም ውሳኔው በጊዜያዊነት መታገዱንና ፍርድ ቤቱም ከእስር በተጨማሪ ለተበዳይዋ የ 60,000 ዩሮ (71,000 ዶላር) ካሳ መወሰኑን ጋዜጣው ጨምሮ አውስቷል። 

ሮቢንሆ የእግር ኳስ ህይወቱን የሀገሩን ሊግ በ 2002 እና 2004 ባነሳበት ሳንቶስ የጀመረ ሲሆን ያሳየው ብቃትም በ 2005 ወደ ሪያል ማድሪድ አምርቶ እንዲጫወት ቢያስችለውም ከሶስት አመት በኋላ የጊዜው ሪከርድ በሆነ 32.5 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ሲቲን ተቀላቅሏል።

Advertisements