ፖል ፖግባ / የቀያይ ሴጣኖቹ ምሰሶ የጉዳት ላይ ቆይታና ዳግም ወደሜዳ መመለስን በተመለከተ ትኩረት የሚሹ ፅንፍ ትርክቶች


ጆሴ ሞውሪንሆ ብዙ ጊዜያት ስለተጫዋቾች ጉዳት አንስተው ሲያማርሩ አይስተዋልም። ነገርግን የኦልትራፎርዱ አለቃ ባለፉት ቅርብ ሳምንታት ውስጥ ቡድናቸው በፖል ፖግባ አለመኖር እጅጉን መጎዳቱን ደጋግመው መግለፃቸው አይረሳም። ይህ የፖርቹጋላዊ የኦልትራፎርድ አለቃ ሀዘኔታም ፖግባ በሜዳ ላይ ሲኖርና ሳይኖር ካለው ፅንፍ ትርክቶች አንፃር ትክክል መሆኑን የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለ በቀጣዩ ፅሁፉ ሊሞግተን ቁጥሮች እና ሌሎች ማወዳደሪያዎችን እያነሳ በዩናይትድ ቤት የፈረንሳዊውን ተጫዋች የሜዳ ላይ ተፅዕኖ እንደሚከተለው ይነግረናል። 


በሚኪያስ በቀለ

በጊዜው የአለም ክብረ ወሰን ዋጋ የላንክሻየሩን ክለብ የተቀላቀለው የኦልትራፎርዱ ኮከብ መስከረም መጀመሪያ ላይ ቡድኑ ከባሴል ጋር በነበረው የቻምፒዮንስ ሊግ ትንቅንቅ የደረሰበት የጅማት ጉዳት ያለፉትን ሁለት ወራት ከሜዳ ውጪ አድርጎት ሲቆይ ቡድኑንም ለከፋ ጉዳት አጋልጦታል።  

ፖግባ በጉዳት ከሜዳ ውጪ ለመቆየት በተገደደበት ሁለት ወራት ውስጥ ዩናይትድ ከነበረበት የፕሪምየር ሊጉ ከፍታ በስምንት ነጥብ ተንሸራቶ መሪነቱን ለምንግዜም ተቀናቃኝ ጎረቤቱ አስረክቦ ማንችስተር ሲቲን ሽቅብ ለመመልከት ተገዷል። 

በነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ዩናይትድ የተነጠቀው የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ግስጋሴውን መሪነት ብቻ አይደለም። ከሁሉም በላይ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ወቅት ያሳየውን ተስፈኛ አጨዋወት ጭምር ለማጣት ተገዶ ታይቷል። ዩናይትድ ፖግባ ባለበትም ከፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ወደኋላ አፈግፍጎ የሚጫወት ተደርጎ ቢተችም የፈረንሳዊው አለመኖር ጉዳት በግልፅ ቡድኑ ላይ ታይቷል።

ውዱ የቡድኑ አማካኝ ከኒማኒያ ማቲች ጋር በጥምረት ባለበት ጨዋታ ዩናይትድ አራት አሸንፎ አንዱን በአቻ ውጤት ሲፈፅም በየጨዋታው የ 2.6 አማካኝ ነጥብ በማግኘት ፖግባ በሌለበት ዘጠኝ ጨዋታ ደግሞ ሁለት ጨዋታ ተረቶ እና አንድ አቻ ወጥቶ የ 1.85 አማካኝ ነጥብን ብቻ በየጨዋታው በማሳካት ትልቅ የአቋም መውረድን አስመዝግቧል።

ዩናይትድ ፖግባ በሌለበት ኳስን በቡድኑ ለማቆየት የነበረበትን ትልቅ የአጨዋወት ችግር እና ሌሎች የስብስቡን አጨዋወት መንገድ ማወዳደር ወደጎን ብንልና በውጤት ደረጃ ብቻ ብንመዝነው እንኳን ፈረንሳዊው አማካኝ በነበረበት ጨዋታ ዩናይትድ ያስመዘገበውን የውጤት ስኬት እሱ በሌለበት ጨዋታ አስቀጥሎ ተጉዞ ቢሆን በዚህን ሰአት የኦልትራፎርዱ ክለብ ከደርቢ ተቀናቃኙ ሲቲ የነበረው የነጥብ ልዩነት ስምንት ሳይሆን ሶስት ብቻ ይሆን ነበር።

በሌላ በኩል ግን የዩናይትድ ተከላካይ ክፍል ከፊቱ ሽፋን የሚሰጠው ፖግባ በሌለበት ጨዋታ ብዙም ሲቸገር አልታየም። ከዚህ ይልቅ በውድድር ዘመኑ በሊጉ ላይ አጠቃላይ ስድስት ግቦችን ያስተናገደው የቀያይ ሴጣኖቹ የኋላ መስመር ፖግባ በሜዳ ላይ ባለበት እና በሌለበት ወቅት የተቆጠረበት ግብ ተመሳሳይ ሲሆን እሱም ሶስት ብቻ ነው።

በእርግጥም ዩናይትድ ከገጠማቸው ቡድኖች ጥራት አንፃር ስንመለከተው እሱ በሜዳ ላይ በሌለበት ወቅት ዩናይትድ በየጨዋታው 0.42 ግቦች በአማካኝ የተቆጠሩበት ሲሆን እሱ በተሰለፈበት ጨዋታዎች በእያንዳንዱ የተቆጠሩበት አማካኝ ግብ ብልጫ ያለውና 0.6 ያህል ነው።

እዚህ ላይ ሊረሳ የማይገባው ቁምነገርግን ዩናይትድ ፖግባን ባልያዘበት ጨዋታ ኳስን በማንሸራሸር እና በማጥቃት ረገድ የወረደ መሆኑና ለጥንቃቄ ጨዋታ እጅግ የበዛ ትኩረት መስጠቱ ፈረንሳዊው ኮከብ በሌለበት በመከላከል ረገድ ለነበረው መለስተኛ ጥንካሬ ምክንያት መሆኑን ያሳየናል።  

የሞውሪንሆ ስብስብ ፖግባ በሜዳ ላይ በነበረበት ጨዋታ ያስቆጠረው ግብ በየጨዋታው በአማካኝ 3.2 መሆኑን ስንመለከት እና እሱ ባልተሰለፈበት ጨዋታ የ 1.57 አማካኝ የግብ ስኬት ብቻ እንዳለው ስንረዳ ዩናይትድ ምን ያህል ፖግባ በሜዳ ላይ በሚኖርበት ወቅት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የሚያስችልና ለአይን በመጠኑም ቢሆን ሳቢ የሆነ ኳስን የማንሸራሸር እግር ኳስ እንደሚከተል ማስረጃ ነው።  

ከዚህ በተጓዳኝ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ ስኬት ረገድ ያሉ አሀዞች ውጤትም በዩናይትድ ቤት ተመሳሳይ ነው። የኦልትራፎርዱ ክለብ ፖግባን ባሰለፈበት በእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካኝ ሰባት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ማድረግ ሲችል እሱ በሌለበት 3.85 ብቻ ነው።  

በአጠቃላይ ሙከራዎችን በመፍጠር ረገድ ደግሞ የሞውሪንሆ ስብስብ ፖግባ በሜዳ ላይ በሚኖርበት እና በማይኖርበት ወቅት የእጥፍ ያህል ብልጫ ያለው ልዩነት ያስመዘገበ ሲሆን ፖግባ ሲኖር በእያንዳንዱ ጨዋታ 14.4 አጠቃላይ ሙከራዎችን ሲያደርግ እሱ በሌለበት ሙከራው ሰባት ብቻ ይሆናል።

የቀድሞው የጁቬንቱስ የመሀል ሜዳ ሞተር የዩናይትድ ቤት ተፅዕኖም እንዲህ በቀላሉ መቋጫ ያለው አይደለም። ፖግባ በተሰለፈበት በእያንዳንዱ ጨዋታ የኦልትራፎርዱ ክለብ ለግብ የቀረቡ 3.2 ሙከራዎችን ማድረግ ሲችል እሱ በሌለበት ማሳካት የቻለው ግማሹን ወይም 1.57 እድሎችን ብቻ ነው። 

በኳስ ማቀበል ስኬት ረገድ ደግሞ ዩናይትድ ፖግባ ባለበት እያንዳንዱ ጨዋታ በአማካኝ የ 116 ብልጫ ያለውን የኳስ ቅብብል ማድረግ ሲችል የቅብብል ስኬት መቶኛውም እሱ በሜዳ ላይ ሳይኖር ካለው የ 80 በመቶ ብልጫ ወደ 87 በመቶ የሚስፈነጠር ነው።

በአማካኝ ስፍራ ሁነኛው ቦታ ላይ ደግሞ ዩናይትድ የ 89 ሚሊዮን ፓውንድ ፈራሚውን ባልያዘበትና ተቃራኒዎቹ የፖግባ ፍራቻ በማይገጥማቸው ጨዋታ በእያንዳንዱ የ 50.8 በመቶ የኳስ ማንሸራሸር ብልጫ ሲኖረው ፈረንሳዊው ኮከብ ባለበት ግን ቁጥሩ ተምዘግዝጎ 63 በመቶ ላይ ይቀመጣል። በፖግባ በሌለበት የዩናይትድ ጥንካሬው በየጨዋታው እሱ ካለበት በአምስት ብልጫ ያለው ኳስን ወደሜዳው ሶስተኛ ክፍል ማሻገሩ ላይ ብቻ ነው። 

እዚህ ላይ ግን ከላይ የተጠቀሱት ማነፃፀሪያዎች በሙሉ ቀጥተኛ መንገድን የተከተሉና ዩናይትድ የገጠማቸውን ቡድኖች የወቅቱ የሊግ ደረጃ ከግምት ያላስገባ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ዩናይትድ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች የገጠማቸው ቡድኖች አማካኝ የሊግ ደረጃ 15ኛ የነበረ ሲሆን እሱ ከተጎዳ በኋላ ዩናይትድ ቼልሲ፣ ቶትነሀም እና ሊቨርፑልን አይነት ቡድኖች ሲገጥም ፖግባን ሳይዝ የተፋለማቸው ሰባት ቡድኖች አማካኝ የሊግ ደረጃ 10ኛ ነው።

እነዚህ የቁጥሮቹ ቀጥተኛ ምልከታ እና ማንችስተር የገጠማቸው ተቃራኒዎች ደረጃም ፖግባ በሌለበት የሮሜሉ ሉካኩን መቸገር የሚያሳይ ሲሆን የ 75 ሚሊዮን ፓውንዱ አጥቂ ጥሩ የኳስ ላይ አጣማሪውን አጥቶ መቆየቱን በተመለከተ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። 

በዚህ ረገድ ሉካኩ የአራት ጨዋታዎች የጎል ድርቁን በቀረፈበት ያሳለፍነው ሳምንት የኒውካስትል ግጥሚያ ከፖግባ በጋራ በተጫወተበት አምስት ጨዋታ ያስቆጠረውን ግብ አምስት ያደረሰበት ነበረ። ፖግባ በአማካኝ ስፍራ ላይ በሌለበት ሰባት ጨዋታ ቤልጄማዊው አጥቂ ያስቆጠረው ሶስት ግቦችን ብቻ ሲሆን ይህም በአማካኝ ሲታይም በየጨዋታው 0.42 ግብ ማለት ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ ሉካኩ ወደጎል አክርሮ የመታቸው አጠቃላይ ኳሶች ብዛት ፖግባ በጨዋታ ላይ በነበረበት ወቅት ከነበረው በተቃራኒው በጉዳት ላይ ሳለ በየጨዋታው ከ 4.8 ምት ወደ 2.57 ሲወርድ ያደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ደግሞ ከ 2.2 ሙከራ ወደ 1.28 መውረድ አሳይቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ፖግባ ባለመኖሩ ሉካኩ በግብ ማስቆጠርና በሙከራ ከደረሰበት ነቀፌታ በተጨማሪ በጨዋታ ላይ በነበረው እንቅስቃሴም ትልቅ ትችት እንዲነሳበት ምክንያት ሆኗል። 

በዚህ ረገድም ፈረንሳዊው የቡድኑ አማካኝ በጉዳት ባልበረበት ወቅት የቀድሞ የኤቨርተን አጥቂ ያቀበለው የኳስ ቁጥር እና የኳስ ንክኪ ብዛት አነስተኛ ሲሆን በተቃራኒ ቡድን የግብ ሳጥን የነበረው የኳስ ንክኪም በየጨዋታው ከ 7.8 ወደ 3.42 ማሽቆልቆል አሳይቷል።

ከሳምንታት በፊት ዩናይትድ በቼልሲ በተረታበት ጨዋታ ቤልጄማዊው አጥቂ በሰማያዊዎቹ የግብ ሳጥን አንድ ኳስ መንካት አለመቻሉም ትልቁ ማስረጃ ይመስላል። በፖግባ መመለስም ሉካኩና ሞውሪንሆ ብቻ ሳይሆኑ የዩናይትድ ካምፕ በሙሉ ትልቅ ደስታ ላይ ይገኛል። 

የፖግባን ወሳኝነት ለመረዳትም አንድ ትልቅ ቡድን ትልቅነቱን በሚያረጋግጥለት መልኩ የጨዋታውን ውጤት በመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃ የሚቀይርበትን እና ከዩናይትድ ቤት የጠፋውን ባህል ፈረንሳዊው አማካኝ ገና ከጉዳት በተመለሰበት የመጀመሪያ ጨዋታ ቅዳሜ ከሰአት ኒውካስትል ላይ እውን ማድረጉን ማስታወስ ብቻ በቂ ይሆናል።

የክለቡ አለቃ በቀጣይ የሚያስፈልጋቸው ብቸኛ ነገርም ባንክ የሰበሩበት ኮከብ ዳግም የጦስ ዶሮ ሆኖ በጉዳት ከጨዋታ እንዳይገለል ተስፋ ማድረግና መፀለይ ብቻ ይመስላል። 

      

 ከኒውካስትል ዩናይትድ በነበረው ጨዋታ የፖግባ አሀዛዊ መረጃዎች

ንክኪ – 82 

ያቀበለው ኳስ – 64 

የነጠቀው ኳስ –

በአንድ ለአንድ ግንኙነት ተቃራኒዎቹን የበለጠበት አጋጣሚ – 4 

ወሳኝ ቅብብል – 2

ምት –

ለጎል ያመቻቸው ኳስ – 1

ግብ – 1

Advertisements