ሃዛርድ፡ ሞሃመድ ሳላህ በቼልሲ ዕድል አልተሰጠውም

ኤዲን ሃዛርድ የቀድሞው የቼልሲ የቡድን አጋሩ መሐመድ ሳላህ በሰማያዊዎቹ ቤት ብቃቱን ማስመስከር እንዲችል ፈፅሞ ዕድል እንዳላገኘ ገልፃ፣ ቼልሲ ቅዳሜ በአንፊልድ ከሊቨርፑል ጋር በሚያደርገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከግብፃዊው ተጫዋች ጋር መለያ ለመቀያየር እንዳሰበም ተናግሯል።

ሳላህ በክረምቱ ዳግመኛ ወደፕሪሚየር ሊጉ በመመለስ በ34 ሚ.ፓ ከሮማ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በተሰለፈባቸው 12 ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን በመምራት ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ላይ ይገኛል።

ይህ ድንቅ ብቃቱም የኹዋን ማታ ምትክ ለመሆን ጥር 2014 በ11 ሚ.ፓ ቼልሲን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ የተጨዋቹን የግል ችሎታ ይከታተሉ በነበሩ ሰዎች ላይ አግራሞትን መጫር ችሏል። ተጫዋቹ በውሰት ወደፊዮረንቲና እና ሮማ (በኋላም ይህንኑ ክለብ በቋሚነት በ12 ሚ.ፓ ተቀላቅሏል) ከማምራቱ በፊት በሆዜ ሞሪንሆው የቼልሲ ቡድን ውስጥ መሰለፍ የቻለው በ19 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነበር።

ይሁን እንጂ ሃዛርድ የቀድሞው የክለብ አጋሩ ሁልጊዜም ምን ያህል ክህሎት እንዳለው እንደሚያውቅ ገልፅዋል። ጨምሮም ግብፃዊው ስታንፎርድ ብሪጅን ከለቀቀበት ጊዜ አንስቶ እያሳየ ያለው አስደማሚ የሆነ የብቃት ማንሰራራት እንደሚያስደስተው ተናግሯል።

“አሁንም ድረስ ጓደኛዬ ነው። አሁንም ድረስ እንገናኛለን።” ሲል ሃዛርድ ስለሳላህ ተናግሮ አክሎም “እሱ ጫፍ፣ ጫፍ፣ ጫፍ የደረሰ ተጫዋች ነው። ይህንን ዕድል በቼልሲ አላገኘም። …ምናልባት በአሰልጣኙ ምክኒያት ነው ወይም በሌሎች ተጫዋቾች ምክኒያት ይሆን? አላውቅም።

“እሱ ብቃት ያለው [ተጫዋች] ነው። በዚያን ወቅት [በቡድኑ ውስጥ] እኔ፣ ዊሊያን፣ ኦስካር ነበርን። ስለዚህ ለእሱ ቀላል ነገር አልበረም። ነገር ግን እሱ ያለጥርጥር ጫፍ የደረሰ ተጫዋች ነው። እንደቡድን ያለውን ብቃትም እናውቃለን። እሱ ድንቅ አጥቂ ነው። በመሆኑም በዚህ የውድድር ዘመን በርካታ ግቦችን አስቆጥሯል።

“በልምምድ ላይ ሁሉንም ነገር ማድረግ ይችላል። በጨዋታዎች ላይ እንኳ ይህን ያደርጋል። አንዳንድ ጊዜም ግቦችንም ያስቆጥራል። ስለዚህ ያለውን ብቃት እናውቃለን። እኔም በእሱ ደስተኛ ነኝ። 

“በአንድ ክለብ ውስጥ የማትጫወት ከሆነ መሄድ ይኖርብሃል። [የመጫወት] ዕድል ያስፈልገሃል። እሱም በፊዮረንቲና [ያገኘውን የመጫወት] ዕድልን ተቀበለ። ስለዚህ የመጫወት ዕድሉን በማታገኝባቸው ጊዜያት ማድረግ የሚኖርበትን ነገር በሙሉ አድርጓል። ሁሉም ተጫዋች መጫወትን የሚፈልግ በመሆኑ እሱም ያደረገው የተለመደ ነገር ነው።

“ለሮማ ሲጫወትም ተመልክቼዋለሁ።…ከብሄራዊ ቡድን ጓደኞቼ አንዱ፣ ራጃ ኒያንጎላንም በእዚያ ነው።…እናም በእዚያም ጥሩ ስራ ሰርቷል።

“አሁንም ገና ጫፍ ይደርሳል። እንዲሁም ከሃገሩ ጋር ጭምር ለዓለም ዋንጫ ለመድረስ ጥሩ ስራ ሰርቷል። በሊቨርፑልም ገና ብዙ ይሰራል። በመሆኑም እሱን ልንጠነቀቀው ይገባል ብዬ አስባለሁ። ቅዳሜ ያለጥርጥርም መለያውን [ለመቀያየር] ልጠይቀው እፈልጋለሁ።” በማለት ቤልጂየማዊው  አጥቂ ተናግሯል።

ቼልሲ በሻምፒዮንስ ሊጉ ካራባግን ለመግጠም 5,000 ማይልሶችን ወደአዘርባጃን ተጉዞ ከተመለሰ 72 ሰዓታት ልዩነት በኋላ ቅዳሜ በአንፊልድ ሊቨርፑልን ይገጥማል። በዚህ የጨዋታ መርሃግብርም አሰልጣኙ አንቴኒዮ ኮንቴ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ከፍ ያለ “ክብር” እንደሚገባው ያምናሉ። ነገር ግን ሃዛርድ ሰማያዊዎቹ በአካልም ሆነ በአዕምሮ ዝግጁ እንደሚሆኑ ገልፅዋል።

“እኔ መቶ በመቶ ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ነው።” ሲል ገልፃ “በርካታ ተጫዋቾች በረቡዕው ጨዋታ ላይ አልተጫወቱም። እኔም የተጫወትኩት 60 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። እንዲሁም ንግሎ [ካንቴ]ም ተቀይሮ ወጥቷል። ስለዚህ ምንም እንኳ ጨዋታው የተቀራረበ ቢሆንም ቅዳሜ አዲስ ጉልበት ይኖረናል። 

“እኛ ፕሮፌሽናሎች ነን። ይህን እንዴት እንደምንወጣው እናውቃለን። ሁሉንም ነገር እናደርጋለን። ከድካማችንም እናገግማለን። ይህንንም ቅዳሜ የምናየው ይሆናል። በራስ መተማመናችን ከፍ ያለ ነው። ጨዋታውን ለማሸነፍም ሁሉም ነገር በእኛ ላይ ነው።” ሲል ገልፅዋል።

Advertisements