ሊቨርፑል ከ ቼልሲ / የሁለቱ ታላላቅ ቡድኖች የተቀናጀ ምርጥ 11 ስብስብቀያዮቹ ሊቨርፑሎች ከሳምንታት በፊት በቶትነሀም ከደረሰባቸው ሽንፈት ወዲህ ሶስት ተከታታይ ድል በማስመዝገብ የምርጥ አራት ቦታን አልመው ነገ ምሽት የአምናውን የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ቼልሲ በሜዳቸው ያስተናግዳሉ። ከተጠባቂው ጨዋታ በፊትም የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለ የሁለቱን ቡድኖች የጋራ ምርጥ 11 አውጥቶ እንደሚከተለው ሊነግረን ተዘጋጅቷል።ቲቤት ኮርትዋ (ቼልሲ)

ቤልጄማዊው የግብ ዘብ በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ ምርጥ በረኞች አንዱ ሲሆን ከሊቨርፑል የቦታው ባላንጣ እና የሀገሩ ልጅ ሲሞን ሚግኖሌት ቀድሞ እዚህ ዝርዝር ውስጥ መግባት ያለበት መሆኑ የማያጠራጥር ነው። 

ኮርትዋ በ 2014 ለመጀመሪያ ጊዜ ፒተር ቼክን ከቋሚ ግብ ጠባቂነት ውጪ አድርጎ ቦታውን ከነጠቀው ጊዜ አንስቶ ወጥ ብቃትን እያሳየ ይገኛል።

ሴዛር አዝቤሉኬታ (ቼልሲ)

በዚህ የውድድር ዘመን በሊጉ ላይ ከሊቨርፑል በሰባት ያነሰ ግብ ያስተናገደው ቼልሲ በኋላ መስመር ምርጫው ላይ ተቀዳሚ ተመራጭ ነው። 

አዝቤሉኬታ በሶስትም ተከላካዮች በተዋቀረ የመከላከል አጨዋወት ላይ በቀኝ ተከላካይ መስመር ላይ ጭምር መሰለፍ የሚችል ነው።

ናትናኤል ክላየንን በጉዳት የማይዘው ሊቨርፑል በዚህ ቦታ ላይ ወጣቶቹን ጆኤ ጎሜዝና ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድን ለማሰለፍ የሚገደድ መሆኑ በምርጥ 11 ስብስብ ውስጥ አዝቤሉኬታን እንድናስቀድም ያስገድደናል።

አንድሬስ ክርስቲንሰን (ቼልሲ)

የ 21 አመቱ ታዳጊ ለሁለት አመታት በውሰት በቆየበት ቦሩሲያ ሞንቹግላድባህ ጥሩ የመሀል ተከላካይ ሆኖ ተመልሷል። ክርስቲንሰን በቋሚነት በትልቅ ደረጃ የመጫወት ሂደቱ በጉዳትና በቅጣት ቢስተጓጎልም በቼልሲ ቤት ከዴቪድ ሊውዝ በልጦ በቋሚነት እየተሰለፈና ቦታው እንደሚገባው እያስመሰከረ ይገኛል። 

ጁኤል ማቲፕ (ሊቨርፑል)

ካሜሮናዊው ተጫዋች ከቀያዮቹ ቤት ተከላካዮች በትልቁ የመተማመን ስሜት የሚፈጥር ሲሆን በዚህ የተነሳም የረጅም ጊዜ ልምድ ካለው ጋሪ ካሂል ቀድሞ ይህን ቦታ አግኝቷል።  

የሎቭረን እና ራግነር ክላቫን ወጥ አቋም አለማሳየት ማቲፕ ለሊቨርፑል ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከሜዳ ውጪ ከሆነበት ሂደት በኋላ ክሎፕ በነገው ጨዋታ ብቁ ሆኖ እንደሚሰለፍላቸውም ተስፋ አድርገዋል። 

ማርኮስ አሎንሶ (ቼልሲ)

ስፔናዊው ተጫዋች ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በነበረው የቼልሲ የዋንጫ ስኬት ውስጥ ከነበሩ አስገራሚ የሜዳ ላይ ጀግኖች አንዱ ነው። 

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አስቸጋሪ ጅማሮን ካደረገ በኋላ ኮንቴ ወደ ግራ ተከላካይ ሚናውን የቀየሩበት አጋጣሚ ምቾት የሰጠው ሲሆን ያለው የመፈፀም ብቃትም በሊቨርፑል ቤት በዘንድሮው የውድድር ዘመን ትልቅ መሻሻል ካሳየው አልቤርቶ ሞሬኖ ቀድሞ በዚህ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ሴስክ ፋብሬጋዝ (ቼልሲ)

የቀድሞው የአርሰናልና ባረወሴሎ አማካኝ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ለኮንቴ አጨዋወት አልመች ብሎ ቢቆይም በውድድር ዘመኑ የመጨረሻ አጋማሽ ብቃቱን በሚገባ ማስመስከር ችሏል።

የዘንድሮው የውድድር ዘመን የቼልሲ ሰሞነኛ የማሸነፍ ግስጋሴም በአብዛኛው በእሱ የፈጠራ ብቃት የመጣ እንደሆነ እየታየ ነው። 

ንጎሉ ካንቴ (ቼልሲ)

ያሳለፍነው አመት የፕሪምየር ሊጉ ምርጥ ተጫዋች በየትኛውም የአውሮፓ ስብስብ ውስጥ ቦታ ማግኘት የሚችል ነው። 

ፈረንሳዊው አማካኝ ያለው አይደክሜነት እና ቁርጠኝነት ሁሌም ቡድኑ እየተንቀሳቀሰ የተቃራኒውን ስብስብ የጨዋታ ሂደት እንዲከታተል የሚያደርግ ውጤታማ አጨዋወት የሚፈጥር ነው።

መሀመድ ሳላ (ሊቨርፑል)

የቀድሞው የቼልሲ ቤት ተገፊ ባሳለፍነው የክረምት በ 34 ሚሊዮን ፓውንድ የክለቡ ሪከርድ ዋጋ ወደ አንፊልድ ከመጣ ወዲህ የዝውውር መስኮቱ ምርጥ ፈራሚ የሚል የአድናቆት ስያሜን ከወዲሁ እየጎረፈለት ሲሆን የተወሰኑ የቼልሲ ደጋፊዎችም የክለቡ ሀላፊዎች ለምን መሀመድ ሳላን እንደ ኬቨን ዴብሩይ እና ሮሜሉ ሉካኩ በቀላሉ እንደለቀቁት በግርምት እየጠየቁ ይገኛል። 

ኤደን ሀዛርድ (ቼልሲ)

የቤልጄማዊው ጨዋታ አቀጣጣይ ምጥቁነት ለአመታት በፕሪምየር ሊጉ ላይ የተመሰከረ ሲሆን በውድድር ዘመኑ ጅማሬ ላይ በመላ ቡድኑ ላይ ከደረሰ መንሸራተት ጋር በተያያዘ መውረድ የታየበት ከመሆኑ ውጪ በቅርቡ እያሳየው የነበረው ብቃትም ለምርጥነት የቀረበ ነበር።

ሳዲዮ ማኔ ያለምንም ጥርጥር አደገኛ ተጫዋች ቢሆንም ለጨዋታ ብቁ ሆኖ የመገኘት ችግር የነበረበት መሆኑ ዘንድሮም በድጋሚ ከጨዋታ ውጪ እያደረገው ከመቀጠሉ ጋር በተያያዘ ከዚህ የምርጥ 11 ዝርዝር ለመፋቅ በቅቷል።

ፊሊፕ ኩቲንሆ (ሊቨርፑል)

ኩቲንሆ የውድድር ዘመኑን በጀርባ ህመምና ከባርሴሎና የዝውውር እሰጣገባ ጋር በተያያዘ ሁነት ታጅቦ ቢጀምርም ብራዚላዊው ኮከብ የዝውውር መስኮቱ ከተዘጋ አንስቶ ወደ ብቃቱ የተመለሰ ሲሆን ባለፉት ጨዋታዎችም ለቡድኑ አምስት ግብ ማስቆጠር ሲችል ሊቨርፑልም እሱ ባለበት የተሻለ አስፈሪ ሆኖ ታይቷል።

ሮቤርቶ ፈርሚኖ (ሊቨርፑል)

ብራዚላዊው ተጫዋች በፊት አጥቂነት ሚና ከአልቫሮ ሞራታ ፉክክር የሚጠብቀው መሆኑና ሁለቱም ጎል ላይ አስፈሪ መሆናቸው እርግጥ ቢሆንም ፈርሚኒዮ አጨዋወቱ ከአማካኝ አጥቂነት ሚና የሚነሳ በመሆኑ ከስፔናዊው የሰማያዊዎቹ አጥቂ የተሻለ የተሟላ ተጫዋች ያደርገዋል።

ፈርሚኖ ያለው ብቃት፣ ከራስ ወዳድነት የነፃ መሆኑና ጠንካራ ሰራተኝነቱ ለተከላካዮች እጅግ አስቸጋሪው የፊት መስመር ተሰላፊ ያደርገዋል።

Advertisements