ሶንግ ደህንነቱን በተመኙለት ሰዎች ፀሎት “ፈጣሪ ችግር ውስጥ” ገብቶ እንደነበር ገለፀ

ካሜሮናዊው የቀድሞው የሊቨርፑል ተከላካይ ሪጎበርት ሶንግ ባለፈው ዓመት ታህሳስ 2009 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ኮማ ውስጥ እንዲገባ ምክኒያት ከሆነውና ህይወቱን በሚያሰጋ የአዕምሮ የደም ዝውውር እክል ህይወቱ አልፎ ቢሆን ኖሮ የእሱን ደህንነት በሚመኙ ሰዎች ፀሎት “ፈጣሪ ችግር ውስጥ ይገባ” እንደናበር ገልፅዋል።

ህይወቱ ማለፏ በማህበራዊ ሚዲያው ሲወረበት የነበረው የ41 ዓመቱ ሶንግ ከቢቢሲው ዎርልድ ፉትቦል ጋር ስለህመሙ ሁኔታ ባደረገው ቃለምምልስ “ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር። አሁን ግን ባለፈው ሳይሆን በዚህች ቅፅበት ላይ እገኛለሁ። ጠቃሚው ነገር በጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘቴ ነው። ደህና ነኝ።” ሲል ገልፅዋል።

ሶንግ ስለህመሙ ክብደት ሲናገርም “ምን እንደተፈጠረብኝ አላወቅኩም ነበር። ፈፅሞ የማውቀው ነገር አልነበረም። በህይወትና ሞት መካከል እየተፋለምኩ እንደነበር እንኳ አላወቅኩም ነበር።

“ነገር ግን [ከሰመመን] ስመለስ ነበር በሆነው ነገር ቀውስ ውስጥ የገባሁት።

“ከጀርባዬ ሰዎች እንደነበሩ የተረዳሁትም ያን ጊዜ ነበር። ሁሉም ሰው የሆነውን ነገር ለማወቅ ፍላጎት ነበረው።” ሲልም የቀድሞው ተጫዋች ሁኔታውን አብራርቷል።  

“እነዚያ ሰዎች በሙሉ ፈጣሪን ችግር ውስጥ ከተውታል። ምክኒያቱም ሁሉም በሁኔታው ሲፀልዩ ነበር። ፈጣሪ ችግር ውስጥ ገባ ብዬ ያስበኩትም በዚህ ምክኒያት ነበር።” ሲል ሶንግ መልካሙን እንዲገጥመው የተመኙለት ሁሉ ህይወቱን እንዳተረፉለት ተናግሯል።

“ሁሉም ሰው “እባክህ ፈጣሪ ያን አታድርግ፣ ሪጎበርትን አትውሰድው’ ብሎ ሲፀልይ ነበር። እንድመለስ ላደረጉኝ በሙሉ አመሰግናለሁ። ተመልሻለሁም። አሁን ዝግጁ ነኝ። የተሟላ አቅም ላይ እገኛለሁ። ስራዬንም እየሰራሁ እገኛለሁ።” ብሏል።

እ.ኤ.አ. በ1994 ለጀርመኑ ክለብ ሜንዝ በመፈረም የአውሮፓ እግርኳስን የተቀላቀለው ሶንግ ከሊቨርፑል በተጨማሪ በሳሌርኒታና፣ ዌስትሃም፣ ኮሎኝ፣ ሌንስ፣ ጋላታሳራይ እና ትራቦንስፖር ክለቦች 417 ጨዋታዎችን ሲያደርግ ለካሜሮን ብሄራዊ ቡድን ደግሞ በ137 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል።

Advertisements