“ጆሴ ሞውሪንሆ ከማንችስተር ዩናይትድ መለያ በተቃራኒው ተከላክሎ ይጫወታል” – ኤሪክ ካንቶና 

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ዝነኛ ተጫዋች ኤሪክ ካንቶና ጆሴ ሞውሪንሆን አድንቆ ነገርግን የፖርቹጋላዊው ስብስብ የፔፕ ጋርዲዮላውን ሲቲ አይነት የማጥቃት አጨዋወት ቢከተል ፍላጎቱ እንደሆነ ተናግሯል። 

ከ 1992 -1997 ድረስ ለአምስት አመታት ለዩናይትድ የተጫወተውና በቀያይ ሴጣኖቹ ቤት ዘመን የማይሽረው ትልቅ ተፅዕኖ ማሳደር የቻለው ፈረንሳዊው ሰው ሞውሪንሆን “ማሸነፍን አጠናክሮ የሚቀጥል አሸናፊ” ሲል አድንቋል።    

በሌላ በኩል ካንቶና ከቢቢሲ አራት የሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረገው በዚህ ቆይታ “እሱ ከማንችስተር ዩናይትድ መለያ በተቃራኒ የመከላከል መንገድን ይከተላል።” ሲል የኦልትራፎርዱ የወቅቱ አለቃ የቡድኑን ባህል እያጠፉ እንደሆነ ገልጿል።

በመቀጠልም በሞውሪንሆ የአሰልጣኝነት ቦታ ጋርዲዮላ እንዲተካ ፍላጎት እንዳለው ለቀረበለት ጥያቄ “ማንችስተር ዩናይትድ ልክ እንደ ባርሴሎና አይነት ነው። ሞውሪንሆን እወደዋለሁ። ያለውን ግርማ ሞገስ እና ጉብዝናውን እወድለታለሁ።

“ጋርዲዮላንም እወደዋለሁ። ሁለቱም ታላላቅ ናቸው። ነገርግን የእኔ ምርጫ አጥቅቶ መጫወት እና ፈጠራ ላይ ያመዘነ አጨዋወት ነው። በእግር ኳስ ዘመኔ በሙሉ ያሳለፍኩት እንደዛ ለመጫወት ስሞክር ነው።

“ዩናይትድ ክለቤ ነው። እነሱ ከክለብም በላይ የደም ትስስር ያለን ነን። ነገርግን በዚህ ሰአት ጨዋታ ከተመለከትኩ የምመርጠው ፈጠራ ያለበትን አጨዋወት ነው።

“ልክ እንደ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ አይነት አጨዋወት… እንደ ሉካ ሞድሪች ወይም ቶኒ ክሩስ አይነት የቡድኑን ህዋሶች የያዘ ቡድን እወዳለሁ።” ሲል የሁለቱም አሰልጣኞች አድናቂ መሆኑን ተናግሮ አዝናኝ እግር ኳስ ግን ምርጫው መሆኑን አስረድቷል።

ዩናይትድ በፕሪምየር ሊጉ አስደናቂ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ካለው የፔፕ ጋርዲዮላው ሲቲ በስምንት ነጥብ አንሶ በሁለተኛነት የተቀመጠ ሲሆን ከውድድር ዘመን ጅማሮ አንስቶ ካደረገው 20 ጨዋታ በአራቱ ሽንፈት ደርሶበታል። 

በሌላ በኩል ያለፉትን 17 ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ሲቲ ካለፈው ነሀሴ አንስቶ በሁሉም ውድድሮች ላይ 19 ጨዋታዎችን ሳይሸነፍ መዝለቅ ችሏል። 

Advertisements