ሀገረ እንግሊዝ / በጫማ ማሰሪያ ክር ተመስሎ በእግር ኳስ ሜዳዎች እና ሌሎች የስፖርት ስፍራዎች ላይ መካሄድ የጀመረው አስፈሪው ዘመቻ 

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በ13ኛ ሳምንት መርሀ ግብሩ ትናንት ምሽት ዌስትሀምን ከ ሌስተር በማገናኘት አሀዱ ብሎ የሳምንቱን መርሀ ግብር መጀመሩ ይታወቃል። የኢትዮአዲሱ ሚከያስ በቀለም ከፕሪምየር ሊጉ ፍልሚያዎችና ሌሎች የሀገረ እንግሊዝ የተለያዩ ስፖርት ፍልሚያዎች ጀርባ “በጫማ ማሰሪያ ክር” የተሰየመ አንድ አስፈሪ ዘመቻ ተደግሶ መካሄድ መጀመሩን በተከታይ ፅሁፍ በዝርዝር ሊነግረን ተዘጋጅቷል።


በሚኪያስ በቀለ

የአላማው አዘጋጆች “ባለቀለም ወይም  ባለቀስተዳመናማ የጫማ ማሰሪያ ክር” የሚል ስያሜን የሰጡትን ‘በጫማ ክር’ የተመሰለ አስፈሪ ዘመቻ በመላው እንግሊዝ ሊተገብሩ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸውን ቀድመው አስታውቀዋል።

ዘመቻው በዚህ በያዝነው ሳምንት በሚደረጉ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች፣ በራግቢ ሜዳዎች፣ በቅርጫት ኳስ ሜዳዎች፣ በሳይክል ተወዳዳሪዎች፣ አትሌቶች እና ሌሎች ስፖርተኞች ጫማ ላይ ከድምቀት በተጨማሪ ሌላ ከባድ አላማን ሰንቆ ሊታይ የተያዘለትን ቀጠሮ ትናንት ምሽት ዌስትሀም ከ ሌስተር ባደረጉት የሳምንቱ መክፈቻ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አሀዱ ብሏል። 

የዘመቻው አዘጋጅ የሆነው ‘ስቶንዎል’ የተሰኘው ማህበር የጫማ ክሩ የሰነቀውን አላማ ሲገልፀው “የግብረሰዶማውያንን በስፖርት ሜዳ መገለል መቃወም እና እነሱን መደገፍ” መሆኑን አብስሯል። በሌላው የስፖርት ዘርፍ ያለውን ትተን በፕሪምየር ሊጉ ብቻ ብንመለከት ትናንት ምሽት በነበረው የዌስትሀም ከ ሌስተር ጨዋታ አሀዱ የተባለው ግብረሰዶማዊነትን የሚያበረታታው ተግባር በሳምንቱ የመጨረሻ የሊጉ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ከ ሀደርስፊልድ እስከሚገናኙበት ጨዋታ ድረስ ይቀጥላል።

የእንግሊዝ 92 የሊግ ቡድኖች ተሰላፊዎች ጫማ ማሰሪያ ክር በዚህ የግብረሰዶማውያን ቀለም ተቀይሮ ጨዋታዎቸውን ለግብረሰዶማውያን ድጋፍ በመስጠት እያደረጉ ቀጥለዋል።

ይህ አስደንጋጭ አላማን የሰነቀው ዘመቻ ጅማሮውን ወደኋላ አራት አመታት ተጉዞ በ 2013 ያደረገ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ሲሆን እስከአሁን ድረስም ግብረሰዶማዊነትን የሚገልፀው ቀስተዳመናማ ቀለም ያላቸዉ ከ 180,000 በላይ የጫማ ክሮች በእንግሊዝ ተሽጠዋል። 

እዚህ ላይ ለዘመቻው ትልቅ ዝግጅት መደረጉን ማረጋገጫው “ቀስተዳመናማ የጫማ ማሰሪያ ክር” የሚል ስያሜን አግኝቶ በጫማ ማሰሪያ ክር ላይ ትኩረት አድርጎ ተሰናዳ እንጂ የቡድን አምበሎች  የሚያስሩት ጨርቅ፣ የመጫወቻ ኳሶቹ፣ ባንዲራዎቹ፣ ከጨዋታው መጀመር በፊት የቡድን አምበሎች የሚቀያየሩት የየቡድኖቹ አርማ ጭምር በግብረሰዶማዊነት አርማና ቀለም ያሸበረቀ እንደሚሆኑ ታውቋል። 

የሊጉ ቡድኖች በዚህ ሳምንት ጨዋታዎቻቸው አምበሎቻቸው አማካኝነት በአንድ ወቅት ፈርናንዲኖ ሲቲን በአምበልነት ሲመራ ክርኑ ላይ አስሮት እንዲገባ የተደረገውን አይነት በግብረሰዶማውያን መደገፊያ ቀስተዳመናማ ቀለም ያሸበረቀ የአምበልነት ምልክት የሚያስሩ ይሆናል።

ግብረሰዶማዊነት በስፋት በሚቀነቀንበት በዚህ ዘመቻ የብሪቴን ቅርጫት ኳስ ማህበር፣ የብሪቴን የኦሎምፒክ ማህበር፣ የብሪቴን የብስክሌት ማህበር፣ የእንግሊዝ ሆኪ ስፖርት ማህበር፣ የእንግሊዝ ራግቢ ፌደሬሽን፣ የእንግሊዝ ክሪኬት ቦርድ፣ የእንግሊዝ እግር ኳሰ ሊግ ማህበር፣ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር፣ የታላቋ እንግሊዝ ራግቢ ማህበር፣ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ማህበር፣ የስኮትላንድ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ማህበር፣ የታላቋ እንግሊዝ አትሌቲክስ ማህበር እና የዌልስ እግር ኳስና ራግቢ ማህበር አላማውን ደግፈው እየተሳተፉ ይገኛል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁሉም በሚባል መልኩ 92ቱም የሊጉ ክለቦች በዚህ በሳምንቱ መጨረሻ በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ቀስተዳመናማ የአምበልነት የክርን ጨርቅ፣ ቀስተዳመናማ የጫማ ክር፣ ዘመቻውን የሚገልፅ ማስታወቂያ እና ቀስተዳመናማ ቀለም ያለው የማዕዘን መምቻ ባንዲራ ይጠቀማሉ።

ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከቦስኒያና ሄርዞጎቪኒያ ጋር የተጫወቱት የእንግሊዝ ሴት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በበኩላቸው ትናንት ምሽት በጨዋታው ላይ ቀስተዳመናማ ቀለም ያለው የጫማ ማሰሪያ ክር አድርገው ወደሜዳ ገብተው ታይተዋል።

አብዛኛዎቹ የእንግሊዝ ሆኪ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች በዚህ ሳምንት ጨዋታዎቻቸው ቀስተዳመናማውን የጫማ ክር አድርገው ወደሜዳ ለመግባት ሲስማሙ የታላቋ እንግሊዝ የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ደግሞ ቀስተዳመናማውን የጫማ ክር በጨዋታ ላይ ከመጠቀም በተጨማሪ በልምምድ ላይ የግብረሰዶም መገለጫ ቀለም ባላቸውን ኳሶች እየተገለገሉ ይገኛል።  

የማንችስተር ዩናይትድ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ የማህደር ማዘመኛ ምስል (profile picture) ዘመቻውን በሚደግፍ ፎቶ እንዲህ አሸብርቃል።

ከሜዳ ውጪ ደግሞ አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ የስፖርት ተቋማት እና ሌሎች አካላት የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸው ዘመቻውን እንዲያስተዋውቁ ጥቅም ላይ እያዋሉ ሲሆን ለተከታዮቻቸውም ዘመቻውን እንዲደግፉ የሚጠይቁ መልዕክቶችን በስፋት እየላኩ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የአቪቫ የራግቢ ሊግም የቀስተዳመናማ የጫማ ክር ዘመቻውን ደግፎ ለስኬታማነቱ እየሰራ የሚገኝ ሌላኛው የስፖርት ዘርፍ ነው።

የአርሰናል ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ በተመሳሳይ መልኩ የማህደር ማዘመኛ ምስሉ (profile picture) ዘመቻውን በሚደግፍ ፎቶ ተቀይሯል።

በሌላ በኩል የፕሪምየር ሊጉ፣ የእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ እና የራግቢ ሊግ የጨዋታ ዳኞች ዘመቻውን ተቀላቅለው በወሳኝ የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ቀስተዳመናማ የጫማ ክር ለማድረግ ከወሰኑና ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ አካላት መሀከል ናቸው። እዚህ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድረ እንግሊዝ ግብረሰዶም መሆናቸውን ይፋ ያደረጉት የእግር ኳስ ዳኛ ሬይ አትኪን በስካይ ስፖርት ድረገፅ ላይ ዘመቻውን በማስመልከት ያሰፈሩትን ፅሁፍ መመልከት የጉዳዩን መጠንከር ለማሳየት ተገቢ ይመስላል።  

የስታምፎርድ ብሪጁ ቼልሲ በዘመቻው ተሳታፊ ነኝ ያለ ሌላኛው የፕሪምየር ሊጉ ትልቅ ክለብ ነው።

አትኪንስ በፅሁፋቸው “በዚህ ሳምንት መጨረሻ የቀስተዳመናማ ጫማ ክሮችን አደርጋለሁ። ምክንያቱም በፕሮፌሽናል እግር ኳስ የመጀመሪያው እራሱን ይፋ ያደረገ ግብረሰዶማዊ ዳኛ እንደመሆኔ የግብረሰዶማውያን ከሌላው ማህበረሰብ መቀላቀል እና በስፖርት ውስጥ ያለውን የግብረሰዶም ፍራቻ ለማስቀረት ዘመቻውን መደገፌ ወሳኝ በመሆኑ ነው። 

ከሊጉ ትልልቅ ሰባት ቡድኖች ኤቨርተን ብቻ ሲቀር ሲቲ፣ ሊቨርፑልና ቶትነሀም እንደ ዩናይትድ፣ አርሰናል እና ቼልሲ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ለግብረሰዶማውያኑ እኩልነትን በሚጠይቁና በሚያበረታቱ ምስሎች ይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸውን ቀይረው ታይተዋል።

“… በፊት ላይ ግብረሰዶም ላይ ያለውን ፍራቻ የሚያሳዩ ‘አንተ በጣም ግብረሰዶም ነህ እሺ’ (you’re so gay) የሚሉ አይነት አፀያፊ ስድቦች ያሉባቸውን ጨዋታዎች ዳኝቻለሁ። .. እንደ ወጣትና ልምድ የለሽ ዳኛ በወቅቱ ቋንቋው ምን ተፅዕኖ እንዳለው የማልረዳና እንዴት መጋፈጥ እንዳለብኝ የማላውቅ ነበርኩ። በጊዜው እንዳልሰማሁ ሆኜ አልፋለሁኝ ወይም እራሴን አርቅ ነበር።

“ወደኋላ ተመልሼ ሳስታውሰው እፍረት ይሰማኛል። በዛ ምክንያትም ከምንጊዜውም በበለጠ ለእኔ ጉዳዩ ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ ትምህርት እንዲሰጥ እና ለለውጡ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዲደረጉ ዘመቻ ማድረጌ ወሳኝ ነው።” በማለት በስፖርት ሜዳ ላይ ግብረሰዶማውያን በኩራት የሚቆሙበት ጊዜ እንዲመጣ በትጋት ለመንቀሳቀስ መዘጋጀታቸውን አሳይተዋል።   

በምድረ እንግሊዝ የመጀመሪያው ይፋ የወጡ ግብረዶማዊው የእግር ኳስ ዳኛ አትኪንሰን ለውጥ ለማምጣት ለመፋለም ዝግጁ ነኝ እያሉ ይገኛል።

የዘመቻው አስተባባሪ አካል ለምን ሁነቱን ማስተናበር እንደፈለገ ለመቀስቀሻነት የሚጠቀምበት ዋነኛ ምክንያትም 72 በመቶ ግብረሰዶማውያን የሆኑ የእግር ኳስ ደጋፊዎች በእነሱ ላይ ፍራቻ ባላቸው ሰዎች የመገለል ጥቃት ደርሶባቸዋል የሚለው አንዱ ሲሆን ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ጉዳዩን በማስመልከት በተደረገ አንድ መጠይቅ 63 በመቶ ሰዎች ግብረሰዶማውያን በስፖርቱ ውስጥ ተቀባይነት እንዳላቸው እንዲሰማቸው መደረግ አለበት ብለው ሀሳባቸውን ከመስጠታቸው ጋር በተያያዘ “የቀስተዳመናማ የጫማ ማሰሪያ ክር” ዘመቻ ትክክለኛ አጋጣሚ እንደሆነ የሚገልፅ ነው።

ይህ ዘመቻም የስፖርት ደጋፊውን ያሳተፈ እንዲሆን በማሰብም በውስጣቸውን ከባድ አላማ የሰነቁት የጫማ ክሮች በሁለት ፓውንድ ዋጋ በየድረገፅ ገበያው ላይ በስፋት እየተዋወቁ ይገኛል። ከጫማ ክሮቹ በተጨማሪም ሌሎች ዘመቻውን የሚገልፁ ቁሶች በሽያጭ ላይ ሲሆን ለዘመቻው የስፖርት አፍቃሪው እጁን እንዲዘረጋም በማስታወቂያ መልክ በሰፊው እየተቀሰቀሰ ይገኛል።

እናም ውድ አንባቢያን ዛሬና ነገ በሚደረጉ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ቀስተዳመናማ ቀለም በየቦታው ብትመለክቱ ብዙም አትገረሙ። ምክንያቱም ይህ የሁለት ቀን መርሀ ግብር ከዚህ ቀደም በስፖርታዊ ሁነቶች ላይ በተናጠል እዛም እዛም ከሚደረገው ልፍስፍስ የግብረሰዶማዊነት ዘመቻ በተቃራኒው በጠነከረና ብዙዎችን ባሳተፈ መልኩ በስፖርቱ ሜዳ ላይም የግብረሰዶማዊነቱን ተፅዕኖ ማስፋፊያ ዘመቻውን ለመስጀመር የማብሰሪያ ፊሽካነት ይዘት ያለው ነውና።

Advertisements