ቬንገር ኦዚል ወደባርሴሎና ሊያመራ እንደሆነ ስለሚናፈሰው ወሬ ሃሳባቸውን ሰጡ

የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር አማካኙ መሱት ኦዚል ወደስፔኑ ኃያል ክለብ ባርሴሎና ለመዛወር ስምምነት ላይ እንዳልደረሰ ገልፀዋል።

ባርሴሎና መላውን የክረምት ወቅት የጨዋታ አቀጣጣዩን አማካኝ በክለቡ ውስጥ ለማካተት በከፍተኛ ሁኔታ ይፈልግ የነበረበት ገዳይ የዝውውር መስኮቱ አብይ የመነጋገሪያ ነጥብ ነበር።

ባሉዋግራናዎቹ ለበርካታ ወራት የሊቨርፑሉን ኮክብ ፊሊፔ ኮቲንሆንም በግልፅ ለማስፈረም ይፈልጉ የነበረ ከመሆኑም በላይ ለደቡብ አሜሪካዊው ተጫዋች በተደጋጋሚ ዳጎስ ያለ ዋጋ አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

ሆኖም ካታላኖውያኑ በጥር ወር ኮቲንሆን ለማስፈረም ዳግመኛ ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሎም በከፍተኛ ሁኔታ ይጠበቃል። በቅርብ ሳምንታት የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ከሆነ ዳግሞ ክለቡ ተጫዋቹን ለማግኘት ከሊቨርፑል ፈቃድ ማግኘት ይችል ዘንድ እስከቀጣዩ ክረምት ድረስ ሊጠብቅ ይችላል።

የዚህ ምክኒያቶች ደግሞ ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው ባርሴሎና በአስገራሚ ሁኔታ ድንቅ በሆነ መንገድ የውድድር ዘመኑን መጀመር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ብራዚለዊው ለሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉ ላይ መሳተፉ ምናልባት ኮቲንሆ ወደኑ ካምፕ የሚያመራ ከሆነ በዚህ የውድድር ዘመን በውድድሩ ላይ ለባርሴሎና  መሰለፍ የማይችል መሆኑ ነው። 

በዚህ ምክኒያትም በርካታ የስፔን የህትመት ሚዲያ ውጤቶች እንዳመለከቱት የላ ሊጋው መሪ ከኢሚራትሱ ክለብ ጋር ያለው ኮንትራት እየተጠናቀቀ የሚገኝ በመሆኑ ምናልባት በጥር ወር ዋጋው ሊቀንስ ይችላል ብሎ ወዳሰበው የአርሰናሉን የጨዋታ አቀጣጣይ መሱት ኦዚል ትኩረቱን አዙሯል።

ከሁሉ በለይ ወሳኙ ነገር አርሰናል በዚህ የውድድር ዘመን በቀዳሚው የአውሮፓ ውድድር ላይ የማይሳተፍ መሆኑ ኦዚል በሻምፒዮንስ ሊጉ ለባርሴሎና ሊሰለፍ የሚችል ተጫዋች የመሆኑ ጉዳይ ነው።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የወጡ አንዳንድ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ከሆነ ደግሞ ኦዚል እና ባርሴሎና ተጫዋቹ በካምፕ ኑ በሚኖረው ቆይታ በግላዊ የኮንትራት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህን ወሬ ግን የመድፈኞቹ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር አስተባብለዋል።

ኦዚል ከባርሴሎና ጋር ስላለው የዝውውር ወሬ ጥያቄ የቀረበላቸው ቬንገር “አይደለም።” በማለት ቀላልና ቀጥተኛ መልስ ሰጥተዋል።

አሰልጣኙ አክለውም “እኔ በእዚያ ላይ ሊኖረኝ የሚችለው ቁጥጥር ምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች በሙሉ ከማንም ጋር መነጋገር የሚችሉ ወኪሎች ነው ያሏቸው። ያ ደግሞ ሰዎችን አይረብሻቸውም። ይህን ነገር በተጫዋችነት ዘመናቸው ላይ በሙሉ ይፈጠራል።

“እነሱ (ኦዚል እና በሚቀጥለው ክረምት ኮንትራቱ የሚያበቃው ሌላኛው ተጫዋች አሌክሲስ ሳንቼዝ) ታማኞች ናቸው። ታማኝነታቸው ላይ ደግሞ ጥያቄ አላነሳም።” በማለት ገልፀዋል።

Advertisements