የሩጫ ድግስ / 17ኛው የቶታል ታላቁ ሩጫ የጎዳና ላይ ውድድር ተካሄደ


ከዚህ ቀደም ከነበረው ተሳታፊ ቁጥር ብልጫ ያለውና ክብረ ወሰን ሰባሪ ተሳታፊ የተገኘበት 17ኛው የቶታል ታላቁ ሩጫ የጎዳና ላይ ውድድር ዛሬ ረፋድ ተካሂዷል። 

ከ 40,000 በላይ ተወዳዳሪ እንደተሳተፈበት በተገለፀው የዘንድሮው ፉክክር በወንዶች ሰለሞን ባረጋ ከደቡብ ክልል በአንደኝነት ውድድሩን ሲፈፅም ሞገስ ጥኡመይ ከመሰቦ እና ዳዊት ፍቃዱ በግል በሁለተኛ እና ሶስተኛነት ተከታትለው ገብተዋል።

በሌላ በኩል በሴቶች ዘርፍ በተደረገው ፉክክር ዘበናይ ይመር ከንግድ ባንክ ውድድሩን በአሸናፊነት ስታጠናቅቅ ግርማዊት ገብረዝጊ ከትግራይና ፎተን ተስፋዬ ከመሰቦ በሁለተኛ እና ሶስተኛነት ውድድሩን ፈፅመዋል። 

የውድድሩ አዘጋጆች ስኬታማና ደማቅ እንደነበር በተናገሩለት በዘንድሮው ውድድር የኬንያዋ የ 2016  የ 5,000 ሜትር የኦሎምፒክ አሸናፊ ቪቪያን ቺርዮት እና ለሆላንድ የምትሮጠው ትውልደ ኬንያዋ ሎራን ኪፕላጋት በክብር እንግድነት ከተገኙ መሀከል ይገኙበታል።

የዛሬውን ጨምሮ ላለፉት 17 አመታት በስኬት የተጓዘው ይህ የጎዳና ላይ ውድድር በተሳታፊዎች ቁጥር በአፍሪካ ከሚደረጉ ተመሳሳይ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን በሚቀጥለው አመትም የተሳታፊውን ቁጥር ወደ 50,000 ለማድረስ መታቀዱ ከውድድሩ ይፋዊ ድረገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይህን የዘንድሮውን ውድድር ከዚህ ቀደም ከነበረው ለየት ባደረገው መልኩ ደግሞ ከሩጫው መጠናቀቅ በኋላ ተሳታፊዎቹ ወደየቤታቸው በመሄድ እረፍት ወስደው ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በጊዮን ሆቴል በሙዚቃ ራሳቸውን ዘና እንዲያረጉ የሬጌ የሙዚቃ ድግስን ጭምር ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በዚህ ለአሸናፊዎች 100,000 የኢትዮጵያ ብር በሽልማት መልክ በተበረከተበት ውድድር በአሳዛኝ ሁኔታ በሩጫው መሀከል ሁለት ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው ማለፉቸው ታውቋል።

የ 2010 የቶታል ታላቁ ሩጫ ውድድር ዝርዝር ውጤት 

          የወንዶች ሩጫ ውድድር ዝርዝር ውጤት 

ደረጃ     ስም                ክለብ              የገቡበት ሰአት

 1.  ሰለሞን ባረጋ      ከደቡብ ክልል          28:36.1

 2.  ሞገስ ጡኡመይ    ከመሰቦ               28:38.9

 3.  ዳዊት ፍቃዱ         በግል                   28:51.1

         ሴቶች ሩጫ ውድድር ዝርዝር ውጤት 

ደረጃ    ስም                ክለብ             የገቡበት ሰአት

1. ዘይነባ ይመር         ከንግድ ባንክ          32:30.6

2. ግርማዊት ገብረዝጊ  ከትግራይ            32:32.6

3. ፉተን ተስፋዬ            ከመሰቦ               32:38.9

Advertisements