ሮሜሉ ሉካኩ ከእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ቅጣት ነጻ ሆነ

 

የማንችስተር ዩናይትዱ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ቤልጄማዊው ሮሜሉ ሉካኩ በብራይተኑ ተጫዋች ላይ በሰራው ጥፋት የሶስት ጨዋታ ቅጣት እንደሚቀጣ ቢጠበቅም ከቅጣት ነጻ መሆኑ ታውቋል

ቅዳሜ ምሽት ማንችስተር ዩናይትድ በሜዳው ብራይተንን አስተናግዶ 1 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ አጥቂው ሮሜሉ ሉካኩ የብራይተኑ ተከላካይ ጋኢታን ቦንግ ላይ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሲማታ ታይቷል።

ጥፋቱ በእለቱ ዳኛ ኒል ስዋርብሪክ እይታ ውስጥ ባይገባም በመልሶ እይታ ሉካኩ እግሩን ወደ ኋላ አንስቶ ሁለት ጊዜ ሲራገጥ ተስተውሏል።

በዚህም መሰረት የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር የምስል እይታውን ተመልክቶ የሶስት ጨዋታዎች ቅጣት ሊያስተላልፍበት እንደሚችል ቢነገርም ተጫዋቹ ግን ከቅጣት ነጻ እንደሆነ ታውቋል።

ሶስት ዳኞችን ያካተተው የውይይት መድረክ የምስል እይታውን ለየብቻ ከተመለከቱ በኋላ ተጫዋቹ የሰራው ጥፋት ቀይ ካርድ ያስጠው ስለመሆኑ በአንድ ድምፅ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ከቅጣቱ አምልጧል።

ተጫዋቹ ቅጣቱ ቢተላለፍበት ኖሮ ዩናይትድ ከዋትፎርድ፣አርሰናል እንዲሁም ከከተማቸው ተቀናቃኝ ማን ሲቲ ጋር የሚያደርጉትን ቀጣይ የፕሪምየርሊግ ጨዋታዎች ያመልጠው ነበር።

ከባለፉት 10 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ከጎል ጋር መተዋወቅ የቻለው የ 24 አመቱ ሉካኩ ከቅጣት ማምለጡ ለክለቡ ደጋፊዎች የተዘበራረቀ ስሜት ፈጥሯል።

አንዳንድ ደጋፊዎች ተጫዋቹ እንደ አጀማመሩ ጎሎችን እያስቆጠረ ባለመሆኑ እና በቡድን እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎው አናሳ በመሆኑ ቅጣቱ ተላልፎበት ዝላታን የቋሚ ተሰላፊነቱን እድል ቢያገኝ እንደሚሻል ምርጫቸውን አድርገዋል።

ሌሎች ደጋፊዎች ደግሞ ቡድኑ በቀጣይነት አርሰናል እና ማን ሲቲን ጨምሮ ጠንካራ ጨዋታዎች የሚያደርግ በመሆኑ የጨዋቹ ከቅጣት ነጻ መሆን መልካም ዜና አድርገው ቆጥረውታል።


ውድ የድረገጻችን የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች የተጨዋቹ ከቅጣት ነጻ መሆኑ በተመለከተ ያላችሁ ሀሳብ ምንድነው? በኮሜንት መስጫው ላይ አስተያየቶን ያስፍሩ።


Advertisements