የስኬት መንገዱን መልሶ ማግኘት የተሳነው ኤሲ ሚላን!

7.jpg

ታላላቅ ተጫዋቾች ስማቸውን የተከሉበት የቀድሞ ስመ ገናና የአውሮፓ ታላቅ ቡድን የነበረው ኤሲ ሚላን ታላቅነቱን ዳግም ለመመለስ ተቸግሯል፡፤ከክለብ ባለቤትነት እና አሰልጣኝነት እስከ ተጫዋችቾ ድረስ ለውጥ ያደረጉት ሮሰነሪዎቹ አሁንም በደጋፊዎቻቸው እምነት የታጣበት ቡድን ሆኖ ጉዟቸውን ቀጥሏል፡፡ቀጣዩ ጽሁፍም የዚህን ታሪካዊ ቡድን ወደ ቀደመው ከፍታው እንዳይመለስ እንቅፋት የሆኑበትን ወቅታዊ ምክንያቶች ይነግረናል፡፡


በ ዕዮብ ዳዲ

አሰልጣኞች ለአንድ ቡድን ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡የቡድናቸውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ለይተው በሚከተሉት ፍልስፍና እና ታክቲክ ተጫዋቾቻቸውን በማሰልጠን ውጤት ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡በርግጥ ሁሉም ክለቦች አሰልጣኛቸው ለሚፈልገው ፍልስፍና የሚሆኑትን ተጫዋቾች ለማዘዋወር አቅም ባይኖራቸውም አንድ አሰልጣኝ ባሉት ተጫዋቾች ክለቡን ወደፊት ማስጓዝ ካልቻለ በቆይታው ላይ ፈጣን ውሳኔ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡

በዘመናዊ እግርኳስ የአሰልጣኞች ቆይታ በአብዛኛው በገነቡት ቡድናቸው ላይ ባሳዩት ስኬት ሲመዘን አንዳንድ ቡድኖች ግን አሰልጣኞቻቸው ከሜዳ ውጪ በሚፈጥሩት ተፅእኖ እና ዕቅድ ተማርከው በትዕግስት ሲጠብቋቸው ይታያል፡፡በአንድ ወቅት የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ዌንገር “በአንድ ክለብ ውስጥ በጣም አስፈላጊው አካል አሰልጣኝ ነው፡፡ምክንያቱም የሆነ የተሳሳተ ነገር ቢፈጠር በመጀመሪያ የሚባረረው እሱ ነው፡፡” በማለት በአንድ ቡድን ውስጥ አሰልጣኝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

8.jpg

ሚላን እንደ አሪጎ ሳኪ፣አንቼሎቲ እና ካፔሎ አይነት በታክቲክ ብቃታቸው የላቁ አሰልጣኞች አሰልጥነውት ለስኬት ቢያበቁትም የአሁን የቡድኑ አንዱ ችግር ግን የቡድኑ አሰልጣኝ ቪሴንዞ ሞንቴላ ብቃት ማነስ እንደነበር እየተነገረ ይገኛል፡፡በርግጥም ሞንቴላ ከሌሎች በሴሪኣ ከሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ከሆኑት ከሳሪ፣ፔሊግሪኒ፣እና ስፓሌቲ ደረጃ ላይ እንደማይገኝ እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ቡድኑን ያለፉት አመታት መንሸራተቱን ለማቅናት ክለቡ በአዲስ በቻይናዊ ባለሀብቶች ተይዞ 175 ሚሊየን ፓውንድ ፈሰስ በማድረግ 11 ተጫዋቾችን ማዘዋወር ቢችልም ካለፉት አመታት የተሻለ አጀማመር ማድረግ ተስኖታል፡፡የወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ቪሴንዞ ሞንቴላም በልምድ እና በታክቲክ የላቀ አሰልጣኝ አለመሆኑ ከሮሲኔሪዎቹ ስንብታቸውን የሚገልጸው ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል፡፡፡

የሞንቴላ ቡድን ኳስ ለመቆጣጠር የሚሞክር ቢሆንም አብዛኛዎቹ በጎንዮሽ ቅብብሎሽ በራሱ ጎል ላይ እንዳይቆጠር ጥንቃቄ የሚያደርግ በፈጠራ ያልታደለ እና የጎል እድል የማይፈጥር ቡድን አድርገውት ነበር፡፡በርግጥ 50 ጎል ከተቆጠረበት የ 2014/2015 እንዲሁም 43 ጎል ካስተናገደው የ 2015/2016 ሚላን የተሻለ የኋላ መስመር መገንባቱን እያነሱ እንዲሁም እንደ ዶናሩማ አይነት ወጣት ተጫዋቾችን እድል መስጠቱ በበጎ ጎኑ የሚጠቀሱለት ቢሆንም አብዛኛዎቹ ግን ለቡድኑ የሚመጥን አሰልጣኝ እንዳልነበረ ይስማማሉ፡፡

በሌላ መንገድ ደግሞ በአንድ አመት ውስጥ 11 ተጫዋቾችን ላዘዋወረ ቡድን የቡድን ግንባታ ላይ በመሆኑ ለአሰልጣኙ ጊዜ ሊያስፈልገው እንደሚገባ እያስታወሱ መሰናበቱ አግባብ እንዳልሆነ ቢሟገቱም ወደ ቡድኑ የተዘዋወሩት የተጫዋቾች ጥራት ዝቅተኛ መሆኑን ሲያስቡ አሁንም ቪሴንዞ ሞንቴላን በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ቁጥር እንጂ ጥራት ላይ ትኩረት አለማድረጉን በማመን ብዙ ተጫዋቾች እንዲገቡ እና እንዲወጡ መፍቀዱ ሌላኛው የቡድኑ ችግር እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

ከሌሎች ተፎካካሪ ቡድኖች አንጻር ሚላን ያለው የቡድን ስብስብ ሲነጻጸር በሌሎች ቡድኖች ውስጥ ሰብረው ቋሚ ሆነው ሊጀምሩ የሚችሉ የቡድኑ አራት ተጫዋቾች ብቻ መሆናቸው ሀሳባቸውን የሚሰጡ አልጠፉም፡፡ከእነዚህ ተጫዋቾች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቅሰው ቦኑቺን ሲሆን ግብ ጠባቂው ዶናሩማ እና ሲልቫን በምርጥ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች ስር ያስገቧቸዋል፡፡ቱርካዊው ሀካን ካላሀንጉሉም አራተኛ የቡድኑ ምርጥ ተጫዋች አድርገው ይጠቅሱታል፡፡ሌሎች የክለቡ ተጫዋቾች ግን ሌሎች ተፎካካሪ ቡድኖች ካሏቸው ተጫዋቾች ደረጃ ላይ የማይገኙ ናቸው በሚል በክለቡ ደጋፊዎች እየተተቹ ይገኛሉ፡፡

2.png

ሌላው እንደ ችግር የሚነሳው ቡድኑ ታላላቅ ጀግኖች ተጫዋቾቹን ለመተካት መቸገሩ ነው፡፡በምስሉ ላይ እንደሚታው ቡድኑ 2006 ላይ የነበረው የቡድኑ ስብስብ ጥራት ተመልሶ የሚያገኘው አይመስልም፡፡የአሁኑ ስብስብ ፍጹም ከድሮው በተቃራኒው በአማካይ ተጫዋቾች የተሞላ በመሆኑ የአሸናፊነት ስነልቦና እና ሜዳ ላይ ድፍረት የጎደለው ፈሪ ቡድን ሆኗል፡፡

በቅርቡ ወደ ሳን ፓኦሎ አቅንቶ ከናፖሊ ጋር ከተጫወተ በኋላ ምንም ነጥብ ሳይዝ የተመለሰው ሚላን በሴሪ ኣው እስከ ስድስተኛ ካሉ ቡድኖች ጋር ደካማ ውጤት አስመዝግቧል፡፡15 ጎሎችን ሲያስተናግድ ማስቆጠር የቻለው ደግሞ አራት ብቻ ነው፡፡ከጨዋታው በኋላ የቡድኑ ተከላካይ ቦኑቺ “ቡድኑ የፍርሀት ምልክት ይታይበታል፡፡” ብሎ የተናገረው ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ይህም ቀድሞ እንደ ጋቱሶ፣ካካ እና ፒርሎ ይዞ የነበረው በኳስም ይሁን በጉልበት ጭምርም የበላይ ነበረው ቡድን ከአሁኑ ስብስብ ጋር ሲነጻጸር የሰማይ እና የምድር ህል ልዩነት እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡

6

ይህ የቀድሞ ገናና ክለብ በካልቾፖሊ ቅሌት ከተደቆሰ በኋላ ለማንሰራራት ተቸግሮ ከመግዛት ወደ መሸጥ በማመዘኑ አብዛኛዎቹን ተጫዋቾች በውሰት እየሰበሰበ ውጤት ማምጣት ሳይችል የችግሮች አቅጣጫዎች ወደ ሲልቭዮ ቤርሉስኮኒ ላይ ቢያነጣጥሩም አንጋፋው ጣሊያናዊ ለቻይኖቹ ባለሀብቶች ቦታውን ለቀው ዞር ካሉ በኋላ ቡድኑ በዝውውር መስኮቱ ላይ የነቃ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ነገርግን ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቡድኑ አሁንም ከባላንጣዎቹ ጀርባ ሆኖ የሊግ ውድድሩን ማድረጉን ቀጥሏል፡፡

ክለቡ በውድድር አመቱ መጀመሪያ ላይ ለታላቅ ስኬት ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ባለፉት አራት ወራት ያደረገው ጉዞ ግን አንኳን አመቱን በዋንጫ ሊያጅብ ቀርቶ በዩሮፓ ሊግ ተሳትፎ ማግኘቱን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ነገርግን ዘንድሮም በዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ በመሆኑ አምና የጆሴ ሞሪንሆው ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ቻምፒንስ ሊጉ የተቀላቀለበትን መንገድ አጥብቀው ሊይዙ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ሚላን ከቪሴንዞ ሞንቴላ በኋላስ ምን አይነት ቅርጽ ይኖረው ይሆን?

Advertisements