“ለኳታር የአለም ዋንጫ አዘጋጅነት ድምፅ ለማሰጠት ከ 10 እስከ 15 ሚሊዮን ፓውንድ ለስድስት ሰው በጉቦ መልክ ተዘጋጅቶልን ነበር” – ሊውስ ቤዶያ

የቀድሞው የኮሎምቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሊውስ ቤዶያ የ 2022 አለም ዋንጫ አዘጋጅ መረጣ ወቅት ለኳታር ድጋፍ እንዲሰጡ እስከ 15 ሚሊዮን ፓውንድ የሚደርስ የእጅ መንሻ ጉቦ ለቀድሞ ስድስት የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ባለስልጣናት እንደቀረበላቸው ለኒው ዮርክ ከተማ ፍርድ ቤት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።  

በዚህ የአሜሪካ መንግስት በፊፉ የሙስና ተግባራት ላይ ከወራት በፊት በጀመረው የክስ ሂደት ጥፋተኛ የተባሉት ቤዶያ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ከሆነ ከእሳቸው በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ልምድ የነበራቸው የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ባለስልጣናት በ 2010 በማድሪድ በተዘጋጀ አንድ ድርድር የጉቦ ጥያቄው እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።

የቀድሞው የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ቤዶያ በ 2016 የህይወት ዘመን እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን በአሁኑ ሰአትም ከሙስና ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ መሆናቸውን ባላመኑ ሶስት የቀድሞ የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ባለስልጣናት የክስ ሂደት ላይ ተጠርተው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ኮሎምቢያዊው ተወላጅ በአስተርጓሚ በኩል ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት በ 2010 ግንቦት የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜን ለመከታተል ወደማድሪድ ማምራታቸውን የገለፁ ሲሆን ከዛም አንድ ስሙን ያልጠቀሱት ኳታራዊ “ወሳኝ ግለሰብ” እና የፉልፕሌይ የገበያ ድርጅት ባለቤት የሆነው አርጀንቲናዊው የንግድ ሰው ማሪያኖ ጂንኪስ ሊያግባቧቸው እንደሞከሩ አውስተዋል።  

ባዶያ ግንኙነቱን አጭር አድርገው ቢገልፁትም ካታራዊው ባለስልጣን ከሄደ በኋላ ጂንኪስ ንግግሩን ወደእጅ መንሻ ጉቦ ወሬ እንደቀየረው አስታውሰው እሳቸውን ጨምሮ ለስድስት ወሳኝ የቀድሞ የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ባለስልጣናት ከ 10 እስከ 15 ሚሊዮን በጉቦ መልክ ሊያከፋፍላቸው ሀሳብ እንደነበረው ገልፀዋል።

ነገርግን መጨረሻ ላይ የቀድሞው የኮሎምቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ምስክርነታቸውን በመቀጠል እሳቸውን ጨምሮ ማንኛቸውም ስድስቱ ከዛ በኃላ በጉዳዩ ዙሪያ እንዳልገፉበት የገለፁ ቢሆንም በወቅቱም ማንኛቸውም በፊፋ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ቦታ ያልነበራቸው ስለነበሩ ውጫዊ ጫና ከማሳደር ውጪ በአለም ዋንጫ አዘጋጅነት ዙሪያ ድምፅ የመስጠት ስልጣን አልነበራቸውም።

ቤዶያ የአሜሪካ አቃቢ ህግ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ተፈፅሟል ካለው የ 150 ሚሊዮን ዶላር የሙስና ተግባር ጋር በተያያዘ ክስ ካቀረበባቸው እና ጥፋተኛ ከተባሉ 40 ሰዎች መሀከል ከሚገኙ በርካታ የቀድሞ የእግር ኳስ ባለስልጣናት እና የገበያ ተቋማት ስራ አስፈፃሚዎች መሀከል አንዱ ናቸው።  

Advertisements