ሌስተር ከ ቶተንሃም | የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቅድመ ቅኝት

የማውሪሲዮ ፖቸቲኖው ቡድን ቶተንሃም በሰሜን ለንደን ደርቢ በአርሰናል ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ ዶርትሙንድን በሻምፒዮንስ ሊጉ በአስደናቂ ሁኔታ በማሸነፍ ጥሩ ማገገም አሳይቶ የነበረ ቢሆንም  በሳምንቱ መጨረሻ በሜዳው ዌምብሌይ ባደረገው ጨዋታ ከዌስት ብሮም ጋር በእጅጉ ተቸግሮ 1ለ1 በመለያየት መልሶ የውጤት ማጣት ችግር ውስጥ ገብቷል።

ሃሪ ኬን አሰልጣኝ የለሾቹ ቤጊሶች ላይ ባስቆጠረው ግብ በ2017 ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ግቦች 40 ከማድረሱም በላይ ከወቅታዊው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው መሐመድ ሳላህ በአንድ ግብ አንሶ በዘጠኝ ግቦች ለወርቅ ጫማው በመፎካከር ላይ ይገኛል። ፖቸቲኖም ስፐርስ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኘውን ማን ሲቲን ጭራ በማንኛውም መንገድ ለመያዝ ሲሉ በተደራራቢ ጨዋታዎች በተጣበበው የበዓል ወቅት ጨዋታዎች ላይ ልዕለ ኮከባቸው የግድ ያስፈልጋቸዋል። የክላውድ ፑየሉ አዲስ ቡድንም በዚህ የውድድር ዘመን በሚደረገው ፉክክር ተገቢውን ፍጥነት ይዞ ለመጓዝ በመቸገር ላይ ይገኛል። ባለንበት ህዳር ወርም ምን ዓይነት ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። ፈረንሳዊው አሰልጣኝም ክለቡ ያለበትን ሁኔታ ማሻሻል እና የቀበሮዎቹ በሊጉ ላይ የነበራቸውን የበላይነት ዳግመኛ ለመመለስ በሊጉ ላይ የተረጋጋ ውጤት ማምጣት የቸገረውን ቶተንሃምን በዛሬ ምሽቱ ጭዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። ሌስሮች ባለፈው የውድድር ዘመን በኪንግ ፓወር ስታዲየም በሊጉ በቶተንሃም 6ለ1 የተሸነፉበትን ጨዋታም ዳግም ፈፅሞ ማስታወስ አይሹም። በዚህ ጨዋታ ቶተንሃም ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ እንዳጠናቀቀ ያረጋገጠበት ከመሆኑም በላይ ኬን አራት ግቦችን በማስቆጠር በአጠቃላይ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች በ26 በማድረስ ለወርቅ ጫማ ፉክክሩ ወሳኝ ቦታ ላይ እንዲቀምጥ አስችሎትም ነበር።

የጭዋታው ቁልፍ ፍልሚያ

ሃሪ ማጓየር ከ ሃሪ ኬን
በዚህ ጨዋታ ላይ ይፈጠራል ተብሎ የሚጠበቀው ቁልፍ ፍልሚያ በሁለቱ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አጋሮች ኬን እና ማጓየር መካከል የሚኖረው ፈክክር ነው። ሌስተር በዛሬው ጨዋታ ሶስት ነጥቦችን ማግኘት እና ዳግመኛ አለመሸነፍ የሚሻ ከሆነ እንግዲያውስ ከምን በላይ በቀዳሚነት የማውሪሲዮ ፖቸቲኖውን ብቸኛ ቁልፍ ተጫዋች የሆነውን ሃሪ ኬንን እንቅስቃሴ እንዲገድብ ተከላካይ ክፍሉን የግድ ጠንካራ ማድረግ ይጠበቅበታል። አለበለዚያ ግን ከወዲሁ ለዳግመኛ የወርቅ ጫማ ፉክክሩ የሚፋለመው እንግሊዛዊ አምበል ቀላል የማይባል ጉዳት እንደሚጠብቃቸው መናገር አይቸግርም። በመሆኑም ማጓየር በጥንቃቄ የኬንን እንቅስቃሴ በማጥናት አጥቂው በግብ ሳጥኑ ዙሪያ በማኛውም ሁኔታ ወደኋላው ዞር ክፍተት በማግኘት ወደግብ እንዳይሞክር ከጀርባ በኩል በአጥቂው ላይ ጫና ማሰደር ይጠበቅበታል። 

የቡድኖቹ ዜና

ዳኒ ሮዝ ከዌስት ብሮም ጋር ባደረጉት የቅዳሜ ጨዋታ በተቀያሪ ወንበር ላይ እንዲቀመጥ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን አሰልጣኙ በተጣበበው የበዓል ወቅት ጨዋታ የመስመር ተከላካዩን ቦታውን መልሶ እንዲያገኝ የግድ ዋሳኔ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል። እንግሊዛዊ ተጫዋች በጥሩ አቋም ላይ ባለመገኘቱም በአሁን ጊዜ ቤን ዴቪስ ለቦታው ተመራጭ ተጫዋች ነው። ቪክቶር ዊንየማ በጉልበት ጉዳት አሁንም በዚህ ጨዋታ ላይ የማይሰለፍ ሲሆን፣ ከሪያል ማድሪድ ጋር በተደረገው ጨዋታ የቋንጃ ጉዳት የገጠመው ቶቢ አልደርዊረልድ ከጉዳቱ ጨርሶ አላገገመም። ነገር ግን ረጅም ጊዜያት ከጉዳት ርቆ የቆየው ኤሪክ ላሜላ በዚህ ጨዋታ ላይ ሊሰለፍ ይችላል። በአንፃሩ በቀበሮዎቹ በኩል ሮበርት ሂዩዝና ማቲ ጀመስ ብቻ በዚህ ጨዋታ ላይ  ዳግም እንማይሰለፉ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

ግምታዊ አሰለለፎች

ሌስተር ሲቲ: ሹሜይክል፣ ሲምፕሰን፣ ሞርጋን፣ ማጓየር፣ ፉክስ፣ ኦልብራይተን፣ ንዲዲ፣ ኢቦራ፣ ግሬ፣ ማህሬዝ፣ ቫርዲ 

ቶተንሃም: ሎሪስ፣ ሳንቼዝ፣ ዳየር፣ ቨርቶንግኸን፣ ትሪፐር፣ ዊንክስ፣ ዴምቤሌ፣ ዴቪስ፣ ኤሪክሰን፣ አሊ፣ ኬን; 

Advertisements