“በእርግጠኝነት ኦዚል ወደ ዩናይትድ ያመራል”  – አያን ራይት

የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ አያን ራይት የቡድኑ አማካኝ ሜሶት ኦዚል በቅርብ ጊዜ ውስጥ የማንችስተር ዩናይትድ ዝውውሩን አጠናቆ ወደ ኦልትራፎርዱ ክለብ እንደሚያመራ ያለውን የእርግጠኝነት መንፈስ ገልጿል። 

ጀርመናዊው የጨዋታ አቀጣጣይ በኢምሬትስ አዲስ የውል ስምምነት ለመፈራረም አሻፈረኝ ከማለቱ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ስሙ ከኦልትራፎርዱ ክለብ ጋር ሲያያዝ ቆይቷል። 

ኦዚል በአርሰናል ያለው ኮንትራት ከአንድ አመት ያነሰ ጊዜ የቀረውና በመጪው ክረምት የሚጠናቀቅ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የኢምሬትሱ ክለብ በሚመጣው ጥር ተጫዋቹን እንደሚሸጥም ይጠበቃል። 

በሌላ በኩል ጆሴ ሞውሪንሆ በይፋ በኦዚል ላይ ያላቸውን ፍላጎት ባይገልፁም ከቀድሞው የሪያል ማድሪድ ኮከብ ጋር በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው እየወጡ ካሉ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል። 

የቀድሞው መድፈኛ ራይትም ጉዳዩን በማስመልከት ለቢቢሲ በሰጠው ቃል ዝውውር የመፈፀሙ ነገር የበዛና በቅርቡ እውን እንደሚሆን ያለውን እይታ አስቀምጧል። 

ራይት ሲናገርም “ሜሶት ኦዚል ወደ ማንችስተር ዩናይትድ ያለቀለት ጉዳይ ይመስላል። ጆሴ ዝውውሩን ለመፈፀም እንደሚወድ እርግጠኛ ነኝ።

“ያም (ዝውውሩ) እንደ ሞት ያስፈራኛል። እሱ (ኦዚል) ትልቅ ተሰጥኦ ያለው እና በዙሪያው ትልልቅ ተጫዋቾች መኖር ይበልጥ ብቃቱን ይጨምርለት ነበር። 

“እርግጠኛ ነኝ ወኪሉና እሱ ለአርሰናል እንዲፈርም ቢፈልጉ ኖሮ ይሄን ያህል ጫና መፍጠር አይፈልጉም ነበር።” በማለት የጀርመናዊው የኢምሬትስ ቆይታ በእሱ መመዘኛ ያበቃለት መሆኑን አስረድቷል።

የቀድሞው የማድሪድ ተጫዋች አርሰን ቬንገር በድንገት መታመሙን ባሳወቁበት እና ባሳለፍነው እሁድ አርሰናል ከበርንሌይ ካደረገው ጨዋታ ስብስብ ውጪ መደረጉ አይረሳም። 

ኦዚል በወቅቱ በርንሌይን ለመግጠም ካመራው ስብስብ ጋር ቢጓዝም በአርሰናል የህክምና ቡድን ወደ ለንደን እንዲመለስ ተደርጓል። 

Advertisements