ንፅፅር / ኤሲ ሚላን ከአንቸሎቲ አንስቶ ባለፉት ስምንት አመታት የቀያየራቸው ስምንት አሰልጣኞች አሀዛዊ ውጤት ምን ይመስላል? 

ከአስር አመታት በፊት የጣሊያኑ ክለብ በአውሮፓ መድረክ አይነኬ ስብስብ መሆን ችሎ ነበር።

የቀድሞ የሳንሲየሮ ነውጠኛ የመሀል ሜዳ ሞተር ጄናሮ ጋቱሶ ቪቼንዞ ሞንቴላን ባሰናበተው ሚላን ያለፉት ስምንት አመታት ታሪክ ዘጠነኛው አሰልጣኝ ሆኖ መሾሙ ብቻ በካካ ፊት አውራሪነት በአንድ ወቅት በአውሮፓ መድረክ ላይ አልቀመስ ብሎ ለነበረው ሚላን ቀውስ ትልቅ ማሳያ ነው። የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለም የሚላንን ምስቅልቅል ከካርሎ አንቸሎቲ አንስቶ በቀጣይ እስከተሾሙት ሰባት አሰልጣኞች ካስመዘገቡት አሀዛዊ ውጤት አንፃር መመልከቱ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል በሚል ዝርዝር መረጃዎችን ሰብስቦ እንደሚከተለው ይዞ ተገኝቷል። 


ሞንቴላ ትናንትና ጠዋት ስንብታቸው ሲረጋገጥ ባሳለፍነው ክረምት ከ 100 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ ከወጣበት የቡድን ግንባታ ሂደት በተቃራኒው ሚላን ከሴሪ አው መሪ ናፖሊ በ 18 ነጥቦች ተንሸራቶ ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ የሰውየውን ስንብት ለከንፈር መጠጣ ጭምር እንዳይመች አድርጎታል። 

ከዛ ይልቅ በዝውውር መስኮቱ ረብጣ ገንዘቦችን እያወጣ ሊኦናርዶ ቦኑቺ፣ አንድሬ ሲልቫ እና ሀካን ካላንጉሉን ወደስብስቡ የቀላቀለው ሚላን በቀድሞ ተጫዋቹ አሰልጣኝነት ስር ይሻሻል ይሆን ወይስ የቁልቁለት ጉዞውን ይቀጥላል የሚለው አሳሳቢ ሆኗል።

በሚላን ቤት ከካርሎ አንቸሎቲ የ 2007 የቻምፒዮንስ ሊግ ስኬት በመቀጠል ለመጀመሪያ ጊዜ ለክለቡ ዋንጫ ማስገኘት የቻሉት ማሲሚላኖ አሌግሪ ብቻ ቢሆኑም እሳቸው በ 2014 ከክለቡ ተሰናብተዋል። 

ባለፉት ሶስት አመታትም ሳንሲየሮ ላይ ውጤት እንደ ሰማይ ሲርቅ ጣሊያናዊው አለቃ ግን አሮጊቷ ጁቬንቱስን ለተከታታይ የሴሪ አ ድልና ሁለት የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ማብቃት ችለዋል።

በአጠቃላይ ከአሌግሪ በኋላ የሚላን ታሪክ እንደ መቃብር ያስፈራል። ባለፋት ሶስት አመታት አምስት አሰልጣኞችን ቀጥሮ ሲያሰናብት አዲሱ ቻይናዊ ባለሀብት ስር ገባ ተብሎ የለውጥ ታሪኩ ጅማሮ እንደደረሰ በቅጡ ገና ሳይወራ ደግሞ ዳግም የውጤት አዘቅት ውስጥ ገብቶ መዳከሩን ቀጥሏል።

ጋቱሶ የፋሽን ከተማውን ክለብ ከአዘቅቱ አውጥቶ ይታደገው ይሆን? የሚለው አሁንም አነጋጋሪነቱን ቀጥሏል። ነገርግን እሱ እስኪታይ ድረስ ከስኬታማው አንቸሎቲ አንስቶ ያለፉትን አስር አመታት በሰንሲየሮ የተፈራረቁትን አሰልጣኞች አሀዛዊ የውጤት ማህደር መዘክዘኩ አይከፋም። 

1. ካርሎ አንቸሎቲ 

ተሾሙ : ህዳር 6፣ 2001

ለቀቁ : ግንቦት 31፣ 2009

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 2762 ቀናት (ሰባት አመት ከስድስት ወር ከ 23 ቀናት) 

የጨዋታ ብዛት : 420

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.94

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 56.67%

ድሎች : ሁለት ቻምፒዮንስ ሊግ፣ አንድ ሴሪ አ፣ አንድ የአውሮፓ የክለቦች አሸናፊዎች አሸናፊ፣ አንድ የፊፋ የአለም ክለቦች ዋንጫ 

2. ሊኦናርዶ 

ተሾሙ : ሐምሌ 1፣ 2009

ተሰናበቱ : ግንቦት 17፣ 2010

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 320 ቀናት (አስር ወር ከ 17 ቀናት) 

የጨዋታ ብዛት : 48

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.71

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 47.92%

ድሎች : ምንም

3. ማሲሚላኖ አሌግሪ 

ተሾሙ : ሰኔ 25፣ 2010

ተሰናበቱ : ጥር 13፣ 2014

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 1298 ቀናት (ሶስት አመት ከስድስት ወር ከ 19 ቀናት) 

የጨዋታ ብዛት : 178

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.81

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 51.12%

ድሎች : አንድ የሴሪ አ ዋንጫ

4. ክላረን ሲዶርፍ

ተሾሙ : ጥር 16፣ 2014

ተሰናበቱ :  ሰኔ 9፣ 2014

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 144 ቀናት (አራት ወር ከ 24 ቀናት) 

የጨዋታ ብዛት : 22

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.59

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 50%

ድሎች : ምንም

5. ፊሊፓ ኢንዛጊ 

ተሾሙ : ሰኔ 9፣ 2014

ተሰናበቱ :  ሰኔ 16፣ 2015

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 372 ቀናት (አንድ አመት ከአንድ ሳምንት) 

የጨዋታ ብዛት : 40

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.38

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 35%

ድሎች : ምንም

6. ሲንሳ ሚሀልጆቪክ

ተሾሙ : ሰኔ 16፣ 2015

ተሰናበቱ : ሚያዚያ 12፣ 2016

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 301 ቀናት (ዘጠኝ ወር ከ 27 ቀናት) 

የጨዋታ ብዛት : 37

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.78

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 50%

ድሎች : ምንም

7. ክርስቲያን ብሮቺ

ተሾሙ : ሚያዚያ 13፣ 2016

ተሰናበቱ :  ሰኔ፣ 2016

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 78 ቀናት (ሁለት ወር ከ 17 ቀናት) 

የጨዋታ ብዛት : 7

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.14

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 28.57%

ድሎች : ምንም

8. ቪቼንዞ ሞንቴላ 

ተሾሙ : ሐምሌ 1፣ 2016

ተሰናበቱ : ህዳር 27፣ 2017

የአሰልጣኝነት ቆይታ : 514 ቀናት (አንድ አመት ከአራት ወር ከ 27 ቀናት) 

የጨዋታ ብዛት : 64

በእያንዳንዱ ጨዋታ ያስመዘገቡት ነጥብ : 1.75

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : 50%

ድሎች : ምንም

አዲሱ ተሿሚ : ጄናሩ ጋቱሶ

ተሾመ : ህዳር 27፣ 2017

የአሰልጣኝነት ቆይታ : ??

የጨዋታ ብዛት : ??

በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚያስመዘግበው ነጥብ : ??

የማሸነፍ ምጣኔ በመቶኛ : ??

ድሎች : ??

Advertisements