አስደናቂ ምሽት / ጁቬንቱስ ነግሶ ባመሸበት የጣሊያን እግር ኳስ የሽልማት ስነስርዓት ጂያንሉጂ ቡፎን የሴሪ አው የአመቱ ኮከብ ተጫዋችነትን ክብር ተቀዳጀ

ጁቬንቱስ ነግሶ ባመሸበት የግራን ጋላ ዴል ካልቺዮው የሽልማት ምሽት ጁያንሉጂ ቡፎን የጣሊያን ሴሪ አ የአመቱ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን ተቀዳጅቷል። 

በቅርቡ ከብሔራዊ ቡድኑ በአሳዛኝ አጨራረስ ጡረታ የወጣው ዝነኛው ግብ ጠባቂ በሀገሩ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፋሽን ከተማዋ ሚላን ላይ በተዘጋጀው የሽልማት ዝግጅት በ 2016-17 ላሳየው አስደናቂ ብቃት የአመቱ ኮከብ ተጫዋችነትን ሽልማት አግኝቷል።

በዚህ ትናንት ምሽት ሰኞ በተደረገውና በሴሪ አው ኮከቦች በደመቀው ዝግጅት ላይ የማሲሞ አሌግሪው አሮጊቷ ጁቬንቱስ በነጠላም ሆነ በቡድን ደረጃ ትልቅ ብልጫን ይዞ ሽልማቶቹን ጠራርጎ መውሰድ ችሏል። 

በዚህም መሰረት በአመቱ የሴሪ አው ምርጥ ቡድን ምርጫ ቡፎን፣ ዳኒ አልቬዝ፣ ሊኦናርዶ ቦኑቺ፣ አሌክስ ሳንድሮ፣ ሚራልም ፒጃኒክ፣ ጎንዛሎ ሄግዌን እና ፓውሎ ዳይባላ የመሰሉ ሰባት ተጫዋቾች በማስመረጥ ጁቬንቱስ በአመቱ ምርጥ ስብስብ ቀዳሚው ተወካይ መሆን ችሏል።

የቱሪኑ ክለብ እንደ ቡድን የነገሰበት የአመቱ ምርጥ 11 ስብስብ አራት ተጫዋቾችን ብቻ ከሌላ የሴሪ አው ክለቦች አካቷል።

ከቱሪኑ ክለብ ተጫዋቾች የተረፉትን አራት ስፍራዎች ደግሞ በአመቱ በቦታቸው ምርጥ ብቃት ማሳየት የቻሉት ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ራጃ ኒያንጎላን፣ ማርክ ሀምሲክ እና ድራይስ ማርቲንስ መቆጣጠር ችለዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም አሮጊቶቹ ክሮቶኔን 3-0 በሆነ ውጤት በረቱበት እሁድ ማግስት በተደረገው በዚህ የሽልማት ስነስርዓት ለስድስት ተከታታይ ጊዜ የሴሪ አው ምርጥ ክለብ የሚለውን ክብር ዘንድሮም መውሰድ ችለዋል። 

ባሳለፍነው ክረምት ወደፓሪሱ ክለብ ፒኤስጂ ያመራው ዳኒ አልቬዝ በምርጥ 11 ስብስቡ ከተካተቱት አንዱ ነው።

ጁቬንቱስ በወቅታዊው የሴሪ አው የደረጃ ሰንጠረዥ ከመሪው ናፖሊ በአራት ነጥቦች ርቆ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በመጪው አርብም ወደ ስታዲዮ ሳን ፖኦሎ አምርቶ ልዩነቱን ለማጥበብ ይጫወታል።

ከሊጉ መሪ ናፖሊ ጋር ከሚያደርገው ትንቅንቅ በመቀጠልም በሁለት ነጥብ ብልጫ ከላዩ የተቀመጠውንና በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ የሚገኘውን ኢንተር ሚላንን በሜዳው ያስተናግዳል።  

Advertisements