ፕሪምየርሊግ፣ ላ ሊጋ፣ ቡንደስሊጋ ወይስ ሴሪ ኣ?

5

በአለማችን ላይ ካሉት የክለብ ውድድሮች ውስጥ በአውሮፓ ውስጥ ያሉት አራቱ ሊጎችን ያህል ተወዳጅነት ማግኘት የቻለ ሊግ ማግኘት ይቸግራል፡፡እነዚህ ሊጎች ከጊዜ ጊዜ ተወዳጅነታቸው እየጨመረ እግርኳስ ወደ ታላቅ ኢንዱስትሪ በመቀየር ከፍተኛ ረብጣ ዶላሮችን በማሽከርከር ወደር አልተገኘላቸውም፡፡ ታላላቅ ተጫዋቾች የሚያገኙትን ጥቅም፣ ተወዳጅነት እንዲሁም የሚሰጣቸው ትኩረት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቅድሚያ ወደ እነዚህ ሊጎች ማቅናት የመጀመሪያ ፍላጎታቸውም ነው፡፡ ቀጣዩ መረጃ ስለ እነዚህ አራት ሊጎች ለማነጻፀሪያነት የሚቀርቡ የተወሰኑ የሙግት ነጥቦችን ይነግረናል፡፡ለመሆኑ ለእርስዎ ምርጡ ሊግ የቱ ነው ?

ተጫዋቾች የእግርኳስ ህይወታቸው አጭር መሆኑ እድሚያቸው ገፍቶ ጫማቸውን ከመስቀላቸው ቀደም ብለው ለቀጣይ ህይወታቸው በመጨነቅ በእነዚህ ታላላቅ ሊጎች ላይ በመጫወት ዳጎስ ያለ ደሞዝ በማግኘት ቀጣይ ህይወታቸው ያማረ ለማድረግ ያልማሉ፡፡ የብዙ ኮከቦች የቅድሚያ ምርጫም በመሆኑ በክለቦች መካከል ጠንካራ ፉክክር ስለሚደረግ ለተመልካቾች ጥሩ መዝናኛ ሆነው ቀጥለዋል፡፡

በቢልየን የሚቆጠሩ ተመልካቾች እነዚህ አለማችን ኮከብ ተጫዋቾችን ለመመልከት በሳምነቱ መጨረሻ በስታድየሞች በመገኘት አሊያም በቴሌቭዥን መስኮት ላይ በማፍጠጥ ይመለከታሉ፡፡ የአብዛኛዎቹ ሊጎች የጨዋታ መርሀግብር ተመሳሳይ በመሆኑ ተመልካቾች ሁሉንም ለመመልከት ስለማይታደሉ ከሀገራቸው ሰአት ጋር ተስማሚ የሆነውን እንዲሁም በአቅራቢያቸው በቀላሉ በሚያገኙት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉ ጨዋታዎችን ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።

በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበት የነበረው የጣሊያን ሴሪኣ እንደ ጁቬንቱስ፣ ኤሲ ሚላን፣ ኢንተር ሚላን፣ ፓርማ፣ ላዚዮ፣ ሳምፒዶሪያ አይነት በቁጥር ብዙ የሆኑ ተቀራራቢ አቋም ላይ የነበሩ ክለቦች በሚያደርጉት ፍጥጫ ይታወቃል፡፡ ብዙዎቹ ያን ጊዜው የሴሪኣው የጦዘ ፍጥጫ ሲያስታውሱ ከአእምሯቸው የማይጠፋው ፓርማ ነው፡፡ ይህ ክለብ አሁን ቀድሞ ይገኝበት ከነበረው የሀገሪቷ ከፍተኛ ሊግ ላይ ባጋጠመው ፋይናንስ ቀውስ መሳተፍ ባለመቻሉ ከንፈራቸውን መጠውለታል፡፡

ክሪስፖ፣ ካናቫሮ፣ ቬሮን እና ቱራም አይነት ኮከብ ተጫዋቾች በፓርማ መልካም ቆይታ ያደረጉበት የጣሊያን ሲሪ ኣ ከቴክኒክ ይልቅ በተወሳሰቡ የታክቲክ ፍልሚያዎቹ ይታወቃል፡፡ ሴሪኣው ከውጤት ማጭበርበር እንዲሁም ከሀገሪቷ የኢኮኖሚ ዝቅጠት ጋር ተያይዞ ታላቅነቱን ካጣ በኋላ በቀድሞው ውበ ፉክክሩ ዘንድሮ ተመልሶ እንደመጣ ሀሳባቸውን የሚሰጡ በዝተዋል፡፡

ለዚህም እንደ ምሳሌ ለማንሳት ያህል ያለፉት አመታት የሴሪኣው የዋንጫ ባለቤት የነበረው ጁቬንቱስ የአምናው የበላይነቱን በድጋሚ ለማሳየት የተሳነበት በተቃራኒው ደግሞ ከሶስት የማያንሱ ክለቦች ዳግም ማንሰራራት የቻሉበት አመት እንደሆነ በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡ሮማ፣ ናፖሊ፣ ኢንተር እንዲሁም ላዚዮ ፌክክሩን ደማቅ አድርገውታል፡፡

እነዚህ ክለቦች ከሌላው አመት በተለየ ኮከብ ተጫዋቾችን ማዘዋወር በመቻላቸው፣ያላቸውን ተጫዋቾች ኮንትራት ማራዘማቸው፣ እንዲሁም ብቁ የሆኑ አሰልጣኞች መያዛቸው ሴሪኣውን ፉክክር በድጋሜ እንዲመለስ እንዳደረጉት ይታሰባል፡፡ይህን ያስተዋሉ እንዲሁም የኤሲ ሚላን እቅድ የተመለከቱ የዓለማችን እግርኳስ ተመልካቾች ሴሪ ኣው በአሁን ወቅት ከሌሎቹ ሊጎች በተሻለ ቅርጽ ላይ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ፡፡

እንግሊዛዊያን ከላይ የቀረበውን የዘንድሮ የሴሪኣ የበላይነት ማሳያ ነጥቦች በሰሙ ጊዜ ፈገግ ማለታቸው አይቀርም፡፡ሚዲያቸውን እንደ መከታ የሚጠቀሙበት እንግሊዛዊያን በየተመልካቹ ሳሎን በቀላሉ በመግባት የሊጋቸው ውድድር እንዲያድግ አድርገውታል፡፡ ዛሬ የእንግሊዝ ፕሪምርሊግ ከታላላቆቹ ሊጎች ቁኝጮ መሆኑን የሚናገሩ በቁጥር በዝተዋል፡፡ እውን ፕሪምየርሊጉ የአለማችን ሊጎች ቁንጮ ነውን?

6.jpg

በሰውነት ንክኪ፣ በረጃጅም ኳሶች እና በፈጣን እንቅስቃሴ ላይ ያመዘነ እግርኳስ የሚበዛበት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በተለይ በአፍሪካ ከፍተኛ ተከታታይ እንዳለው ይታመናል፡፡ሊጉ ሁልጊዜ አዳዲስ አሸናፊዎችን እያሳየ መሄዱን ቀጥሏል፡፡ በሙሉ ስታድየም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ለማሸነፍ የሚከፈለው መስዋእት ታጅቦ ውጥረት በነገሰበት ሁኔታ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ፡፡ የከዋክብት መኘኻሪያ መሆኑ ሌላው ተወዳጅ እንዲሆን ያደረጉት ምክንያት አንዱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሊገመት የማይችል ውጤት የሚመዘገብበት መሆኑ ብዙዎቹ ዘንድሮም ትክክለኛ ፉክክር የሚደረግበት መድረክ መሆኑን ያምኑበታል፡፡

7.jpg

አለማችን ካሳየቻቸው ኮከብ ተጫዋቾች መካከል የሚካተቱት ሊዮ ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ የሚገኙበት የስፔን ላሊጋ ምንም እንኳን በየአመቱ ሁለት ፈረሶች ፍልሚያ እየሆነ ቢሄድም ሁለቱ ኮከቦች ሊጉ ተመልካች እንዲያጣ አላደረጉትም፡፡ ነገርግን ለአንዳንድ አገራት የጨዋታው ሰአት አመቺ ካለመሆኑ የተነሳ እኩለ ለሊት ላይ የላሊጋውን ጨዋታዎች ለመመልከት በትእግስት የሚጠብቁ በቁጥር አናሳ ናቸው፡፡

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ማድሪድ እና ባርሴሎና ውጤታማ መሆናቸው ብቻ የሊጉን የጥራት ደረጃ የሚያሳይ እንደሆነ በመንገር ላሊጋው ከሌሎቹ የላቀ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ከሰውነት ንክኪ የነጻ በቴክኒካል እንቅስቃሴዎች፣ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞከርበት እና ኳስን መስርቶ የሚጫወት ቡድን የሚታይበት በመሆኑ ትክክለኛው የኳስ አርት የሚታይበት ቦታ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ሮናልዲንሆ በባርሴሎና ቆይታው ከኳስ ጋር ሲደንስ የታየው በስፔን ላሊጋ እንጂ በሌሎቹ ሊጎች አይደለም፡፡ እነ ሮናልዶ ልዊስ ናዛሪዮ ዴሊማ እና ሌሎች የላቲን ተጫዋቾችም በሚገባ ከኳስ ጋር ትርኢት ያሳዩበት የውድድር መድረክ ላሊጋው ብቻ ነው እያሉ የሚሟገቱ ብዙ ናቸው፡፡ክርክራቸውን ጠንካራ እንዲሆን ያደረገ ደግሞ የዚህ አመት የቫሌንሺያ ብቃት መሻሻል ሆኗል፡፡ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአውሮፓ መድረክ ጭምር ጠንካራ የነበረው ቫሌንሺያ ዘንድሮ ዳግም መከሰቱ ለሊጉ ውበት የጨመረ እንደሆነ በማሰብ ለዘንድሮ ላሊጋ ፍልሚያ ቅድሚያውን ሰጥተዋል፡፡

8.jpg

ፍሰት ያለው ኳስ፣ የግል ተሰጥኦ፣ ካማረ ስታድየም ድባብ ጋር የሚታይበት የጀርመን ቡንደስሊጋ ቀድሞ ከነበረው ውበት እያደገ መጥቷል፡፡ በተለይ ባማሩ ስታድየሞች የሚታየው ያማረ የደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ እንዲሁም ክለቦች ለደጋፊዎች የሚሰጡት ክብር ብዙዎቹን ተመልካቾች የሳምንቱን ውድድሮች በናፍቆት እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡

በርግጥ በአመቱ መጨረሻ ላይ አሸናፊውን ለመገመት ከባድ ባይሆንም በየጨዋታው የሚቆጠሩ የጎል ብዛቶች እንዲሁም ወጣት ተጫዋቾች እድል የሚያገኙበት ንጹህ እግርኳስ የሚታይበት ቦታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የወጣት አሰልጣኞች መገኛ ቦታም በመሆኑ የሊጎች ቁንጮ እንደሆነ የሚናገሩ ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡

ውድ የድረገጻችን ተከታታዮች ከአራቱ ሊጎች ለእርሶስ ምርጡ የቱ ነው? ሀሳብዎን በኮሜንት መስጫው ላይ ይግለጹልን፡፡

Advertisements