“መወለድ ከነበረብኝ ሁለት ወራትን ብቀድምም ለመወለድ ዝግጁ ነበርኩ” – ጄናሩ ጋቱሶ


አወዛጋቢ ጄናሩ ጋቱሶ መወለድ ከነበረበት በሁለት ወራት ቢቀድምም ለመወለድ ዝግጁ እንደነበር የሚገልፅ አስገራሚ አስተያየትን ቪቼንዞ ሞንቴላን ተክቶ መሾሙን አስመልክቶ ከነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መጠናቀቅ በኋላ ሰጥቷል።

የቀድሞው የሚላን አማካኝ የሳንሲየሮው ክለብ አሰልጣኙ የነበሩትን ሞንቴላን ከማሰናበቱ ጋር በተያያዘ ከወጣት ቡድን አሰልጣኝነት በቀጥታ ወደዋና ቡድኑ አሰልጣኝነት ሽግግር እንዲያደርግ አስችሎታል።

ጋቱሶ ከጋዜጣዊ መግለጫው ማብቃት በኋላ “አሁን ተረጋግቻለሁ። ለረጅም ጊዜ ግን አይቆይም። በመጪው ጊዜ ከባድ ፈተና ነው።” በማለት በእግር ኳስ ተጫዋችነቱ የነበረው ነውጠኛ ባህሪ ቀዝቀዝ ማለቱን ነገርግን በቀጣይ ተረጋግቶ ለመቀጠል ፈተና እንዳለበት ገልጿል።

ጋቱሶ በመቀጠል አጉሊ መነፅር እና ዳግም የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ለመቆጣጠር እንዲያነሳሳው የተራራ መወጣጫ ጨምሮ የተለያዩ ስጦታዎች የተበረከተለት ሲሆን ሚላን ከሴሪ አው መሪ ናፖሊ በ 18 ነጥቦች መራቁን ለመግለፅም ሙቀት የሚሰጥ ኮት ተሰጥቶታል። 

ጋቱሶ ከስጦታው በኋላ “በእውነት ይሄን ለእኔ ከሆነ ከእኔ ጋር በጋራ ወደተቀያሪ ወንበር እወስዳቸዋለሁ። ታውቃላችሁ መወለድ ከነበረብኝ ሁለት ወራትን ብቀድምም ለመወለድ ዝግጁ ነበርኩ።” በማለት በተበረከተለት ነገር የተሰማውን ስሜት ተናግሯል። 

ከዛም ሞንቴላ ስህተት ሰርተው እንደሆነ የተጠየቀው ጋቱሶ “ብዙም ስህተት አልሰራም። ነገርግን በሂደት ጊዜ እና እድል ትፈልጋለህ። ከ 10-12 አዳዲስ ተጫዋቾች ሲመጡ የተወሰነ ጊዜ (ለማቀናጀት) ትፈልጋለህ። እሱ ለህይወትና ስራ ላለው መንገድ ባርኔጣዬን ከፍ አደርግለታለሁ።” በማለት ለቀድሞ የክለቡ አለቃ ያለውን ክብር አሳይቷል።

በሌላ በኩል ሞንቴላ በሚላን አሰልጣኝነት በቆዩበት ወቅት በ 23 ጨዋታ 23 የተለያየ አሰላለፍን መከተላቸው ያስተቻቸው ቢሆንም “እኔ ከ 24-25 በማድረስ አዲስ የአለም ክብረ ወሰን መስበር እፈልጋለሁ።” በማለት ጋቱሶ በጉዳዮ ለመቀለድ ሞክሯል። 

ጋቱሶ ንግግሩን በመቀጠልም “ሲልቪዮ ቤርልስኮኒ (የቀድሞው የክለቡ ፕሬዝዳንት) ጠርተውኝ ነበር። በጣም ወሳኝ ንግግር ያደረግን ሲሆን በጣም ደስተኛ ነበርኩ። አዲሱ የክለቡ ባለቤትም (ዩንሆንግ ሊ) ጠርተውኝ ነበር። በቅርቡም ፊትለፊት ተገናኝተን እናወራለን።” በማለት የቅጥሩን ሂደት አስታውሶ ተናግሯል።

ከዛም በቻይኒኛ አንድ ቃል ደግሞ እንዲል ተነገረውና ቃሉም “ምንጊዜም ሚላን” (Forza Milan) የሚል መስሎት ደግሞ ካለው በኋላ የቃሉ ትርጉም “ምንጊዜም ኢንተር” (Forza Inter) የሚል መሆኑ ሲነገረው ሁለቱን ጠያቂ ጋዜጠኞች በጨዋታ መልክ ጎሸመ አደረገና ውይይቱ በዛ መልክ አብቅቷል።

Advertisements