ካርሎስ ባካ – “ከአሳ አጥማጅነት እስከ ኮከብ ተጫዋችነት” የተጓዘ አስገራሚ የህይወት ለውጥ!

8.jpg

 

ጠንክሮ መስራት እና ትዕግስት  በሁሉም የሙያ ዘርፍ የሚያስፈልግ የስኬት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ያስተማረ፣ ከኮሎምቢያ ድህነት መንደር እስከ አንዳሉሺያን የቅንጦት ህይወት የተጓዘ፣ የድህነት ቀንበርን በጠንካራ ስራው እና ትዕግስቱ ሰብሮ በማለፍ ህይወትን ማሸነፍ የቻለው የካርሎስ ባካ የህይወት ውጣ ውረድ በሌላ ሙያ ላሉ ሁሉ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡


ዕዮብ ዳዲየዚህ ተጫዋች ታሪክ መሳጭ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ፊልም መቀየርም እንደሚቻል ብዙዎች ሀሳባቸውን ይሰጣሉ፡፡የስኬትን በር ያገኘው አርፍዶ ቢሆንም ጠንካራ ስራው እና ትዕግስቱ ለስኬቱ ትልቁን ሚና መጫወት ችለዋል፡፡

የተወለደው ከ አባቱ ጂሊቤርቶ ባካ እና ከእናቱ ኢሎይሳ አሁማዳ ባራንቂላ በምትባል አካባቢ ሲሆን ከድሀ ቤተሰብ በመገኘቱ ቤተሰቡን ለማገዝ ከልጅነቱ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ከባድ ህይወትን አሳልፏል፡፡

እስከ 20 አመቱ ድረስ በትንሽዋ የትውልድ መንደሩ አሳ አጥምዶ እየሸጠ፣ በትርፍ ሰአቱ ደግሞ የአውቶቢስ ረዳት በመሆን ካለበት መንደር 30 ኪሜ ወደ የምትርቀዋ ከተማ በመመላለስ  ከልጅነቱ ጀምሮ ህይወትን ለማሸነፍ ከጠዋት እስከ ማታ ጉልበቱን ሳይሰስት ላይ ታች ብሏል፡፡

ነገርግን የህይወት ገፅታዋ እንዳሰበው ባይሆንም በውስጡ እንደ እሳት ይንቀለቀል የነበረው ግን  ለእግርኳስ ያለው ልዩ ፍቅሩ ነበር፡፡አሳ ለማጥመድ እንኳን በሚሄድበት ጊዜ በቀኝ እጁ ለአሳ ማጥመጃ የሚያገለግሉት መረብ እና የተለያየ ቁሳቁሶች በእግራ እጁ ደግሞ ኳስ የመያዝ ልማድ ነበረው፡፡

በሀይማኖቱ ጥብቅ በመሆኑ ታዋቂ የአለማችን ተጫዋች የመሆን ህልሙ ሊሳካ እንደሚችል ቢያስብም አልፎ አልፎ ግልፍተኛ ባህሪው ከሩቅ እንደማያደርሰው ህልሙ ከቅዥት ያለፈ እንደማይሆን የሚነግሩት አልጠፉም፡፡

4.jpg

ባካ በ23 አመቱ አትሌቲኮ ጁኒየር ለሚባል ቡድን ሙከራ አድርጎ ክለቡ በተጫዋቹ አቋም በመደሰቱ ምንም እንኳን የዘገየ ምልመላ ቢሆንም የመጀመሪያ የፕሮፌሽናል ኮንትራት አቀረበለት፡፡ነገርግን ህይወት በክለቡ ቀላል ሆኖ አላገኘውም፡፡ በክለቡ ቋሚ ሆኖ የመሰለፍ እድል በማጣቱ 2007 ላይ ወደ መንደሩ ባራንቂላ ላለ ክለብ በውሰት ተላከ፡፡

አዲሱ ክለቡ ግን ከተመሰረተ ረጅም አመት ያልሆነው ስለነበረ መጫወት የቻለው በታችኛው ዲቪዝዮን በሚደረገው ውድድር ነበር፡፡በክለቡም 27 ጨዋታ አድርጎ 12 ጎሎችን በማስቆጠር ጎል ማስቆጠር ብዙ የሚቸገር ተጫዋች እንዳልሆነ አሳየ፡፡ነገርግን አሁንም ከባድ ፈተናው ሁልጊዜ በቋሚነት ተሰልፎ መጫወት አለመቻል ነበር፡፡ወደ ቬንዝዌላም ተልኮ ሚኔርቨን ለሚባል ክለብ ለአንድ አመት በውሰት እንዲጫወት ተሰጠ፡፡ባካ በኮሎምቢያ ቤተሰቦቹን ጥሎ መሄዱ በናፍቆት ቢያንገበግበውም ቡድኑን በፍጥነት በመልመድ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ቻለ፡፡

በአመቱ ያስቆጠራቸው ጎሎችም የቬንዝዌላውን ሚኔርቨን ክለብ ሁለተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ ቻለ፡፡ቢሆንም በውሰት የላከው ክለቡ አትሌቲኮ ጁኒየር ወደ ክለቡ ለመመለስ ፍላጎት ማሳየት ሳይችል ቀረ፡፡ሶስት አመት ቆይታ አድርጎ ወደ ትውልድ መንደሩ ቢሪንቂላ ተመለሰ፡፡

በውሰት መንከራተቱ ተስፋ ቢያስቆርጠውም ህልሙን ለማሳካት በትእግስት ጠንክሮ መስራቱን ያላቋረጠው ባካ በትውልድ መንደሩ ክለቡ አሁንም በቂ እድል ባይሰጠውም በተሰለፈበት አጋጣሚ ጎሎች ማደኑ መደበኛ ተግባሩ አደረገው፡፡በ 19 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 14 ጎሎችን በማስቆጠር ድንቅ አመትን አሳለፈ፡፡

2009 ላይ በአካል ብቃቱ ዳብሮ ወደ አትሌቲኮ ጁኒየር የተመለሰው ባካ እጅግ አስገራሚ አመት በማሳለፍ በኮፓ ኮሎምቢያ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ በማጠናቀቅ ተቺዎቹን አፋቸውን ማዘጋት ቻለ፡፡በቋሚ ተሰላፊነት ሁልጊዜ መጫወቱ ደስተኛ ያደረገው ባካ አቋሙን እያሻሻለ የጎል አነፍናፊ መሆኑን በሚገባ እያስመሰከረ ሄደ፡፡

በአንድ ወቅት ከስፔኑ ማርካ ጋር ቆይታ አደርጎ ስለ ህይወቱ ውጣ ውረድ ሲናገር “በልጅነቴ አስቸጋሪ ጊዜን አሳልፊያለው፡፡ 2009 ላይም በ 23 አመቴ የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል ጨዋታዬን አደረኩኝ፡፡ ነገርግን ገንዘብ ማግኘት ስጀምር ህይወትን እንዳሸነፍኩ ቆጥሬ ነበር፡፡ ነገርግን ሀሳቤ ስህተት ነበር፡፡እዚህ የደረስኩት እራሴን አሳድጌ እና ተሸክሜ ነው፡፡ጀግንነት ማለት ከችግር ጋር አብሮ የሚሰምጥ ሳይሆን ቀና ብሎ ጠንክሮ የሚያሸንፍ ነው፡፡

“በ 20 አመቴ በመንደሬ ውስጥ የመኪና ረዳት ሰራተኛ ሆኜ እኖር ነበር፡፡ህይወት ቀላል አይደለም፡፡በቀጣይነት የአውቶቢስ የትኬት ሰብሳቢ ሆኜ ሰርቻለው። ምክንያቱም እኔ ከድሀ ቤተሰብ የተገኘው በመሆኑ እነሱን መርዳት ነበረብኝ፡፡በዛ እድሜዬ እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን በሩ ተዘግቶብኝ ነበር፡፡” ሲል አስቸጋሪ ህይወቱን ያስታውሳል፡፡

2009 ላይ መልካም አመት ያሳለፈው ባካ እንደ ቼቮ እና ሎኮሞቲቭ ሞስኮ አይነት ክለቦች አይናቸውን በመልማዮቻቸው አማካኝነት ተጫዋቹን መመልከት ጀመሩ፡፡

ሎኮሞቲቭ የተጫዋቹን ፊርማ ለማግኘት ከተስማማ በኋላ ፍሊፔ ካይሲዶን በማስፈረሙ ባካን ወደ  ቤልጄሙ ክለብ ብሩዥ እንዲቀላቀል ፈቃድ ሰጠው፡፡ክለብ ብሩዥ ለዝውውሩ 1.5 ሚሊዮን ዩሮ በመክፈል ለሶስት አመት ማስፈረም ቻለ፡፡በዚህ ጊዜ የኮሎምቢያ ጋዜጦች ተጨዋቹን ከብዙ የውሰት ውል ውጣ ውረድ በኋላ ለስኬት የደረሰበትን መንገድ በመግለጽ ወደ አውሮፓ ማቅናቱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገለጹ፡፡

በቤልጄም በመጀመሪያው ጨዋታ ከጎል ጋር ቢተዋወቅም በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ተጠባባቂ ሆኖ አሳለፈ፡፡ ነገርግን ጎል ማስቆጠር የከበደው ክለብ  ብሩዥ ተመልሶ ባካን በመመልከት ተጫዋቹን አሰልፎ ማጫወት ጀመረ፡፡ ተጫዋቹም ብዙ ጎሎች ጎሎች በማስቆጠሩ ክለቡ የፈለገውን አውሮፓ ክለቦች ተሳትፎን ማሳካት እንዲችሉ እገዛ አደረገ፡፡

በቀጣቹ አመታት በቤልጄም የነገሰው ባካ ሌሎች ታላላቅ ክለቦች ፊርማውን ለማግኘት ይሯሯጡ ጀመር፡፡ነገርግን የተሳካለት የስፔኑ ሲቪያ ነበር፡፡2013 ላይም ኮሎምቢዊውን ተጫዋች የግሉ አደረገ፡፡የተጫዋቹ የስኬት ግራፉ ወደ ላይ ከፍ እያለ 2015 ላይ በዩሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ዲኒፕሮ ላይ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ሲቪያ የዋንጫ ባለቤት እንዲችል አደረገ፡፡በወቅቱ ባካ የዩሮፓ ሊግ አሸናፊ ከሆነ በኋላ ስቅስቅ ብሎ አልቅሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ከጨዋታው በኋላ “አልቅሺያለው ምክንያቱም በጣም ተደስቻለው፡፡ጥሩ ለመጫወት ሁልጊዜ ጠንክሬ ስሰራ ነበር፡፡”ሲል ተናግሯል፡፡በቀጣዩ ዝውውር የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ውል ማፍረሻ ከፍሎ ማዘዋወር የቻለ ሲሆን አሁን በስፔን በቪላሪያል እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ተጫዋቹ ጠንክሮ መስራቱ እንዲሁም ስኬትን ለማግኘት እስከ መጨረሻ ትዕግስተኛ መሆኑ አሁንም ድረስ ሰዎች በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ላይ ጠንክረው እስከ ሰሩ ድረስ እንዲሁም የስራን ውጤት ለማግኘት በትዕግስት ከጠበቁ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያስተማረ ሆኗል፡፡

 

Advertisements