“አስደንጋጩ አቀባበል” – ሬናቶ ሳንቼዝ የራስ መተማመኑ በስዋንሲም አጥቶታል

11 

 

2015 ላይ ገና በ 18 አመቱ የወደፊቱ ኮከብ እንደሚሆን በስፋት ተወርቶለት የነበረው ፖርቹጋላዊው ሬናቶ ሳንቼዝ አሁን እድሜው 20 ቢሞላም ባለፉት አንድ አመት ተኩል ህይወት ዳገት ሆኖበት በጀርመን ቡንደስሊጋ እንዲሁም በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ እራሱን ማግኘት ተስኖታል፡፡

ወጣቱ ተጫዋች 2015/2016 በሀገሩ እና የልጅነት ቡድኑ ከሆነው ቤኒፊካ ጋር ድንቅ አመትን በማሳለፍ ቡድኑ የፖርቹጋል ሊግ እንዲያሸንፍ ትልቅ ሚና መጫወት ችሏል፡፡በቻምፒየንስ ሊጉም እስከ ሩብ ፍጻሜ ድረስ በመጓዝ በወጣትነቱ በታላላቅ መድረኮች ላይ ተሳትፏል፡፡

ተጫዋቹ በወጣትነቱ እያሳየ የነበረው እንቅስቃሴ ለፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን እንዲጠራ ስላገዘው በ2016 ቱ የአወሮፓ ዋንጫ ላይ ሀገሩን ወክሎ በመሳተፍ ፖርቹጋል የውድድሩን ዋንጫ እንድታነሳ ሳንቼዝ ትልቅ ሚናን መጫወት ችሎ ነበር፡፡በተለይ ክሮሺያን በገጠሙበት የጥሎማለፍ ጨዋታ ላይ ኮከብ ተጫዋች የሚያስብል እንቅስቃሴ ሲያሳይ፣ በሩብ ፍጻሜ ደግሞ ፖላንድ ላይ ጎል በማስቆጠር ከፊትለፊቱ ብሩህ ጊዜ የሚጠብቀው ወጣት ተጫዋች መሆኑን በሚገባ አስመስክሮ ነበር፡፡

4.jpg

በመቀጠል ታላላቅ የአውሮፓ ቡድኖች ተጫዋቹን ለማስፈረም ላይታች ቢሉም፣ ወጣቱን ተጫዋች በእጁ ማስገባት የቻለው ግን የጀርመኑ ባየርሙኒክ ነበር፡፡ሳንቼዝ ወደ ሙኒክ ካቀና በኋላ ከመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ጨዋታውን እንዲጀምር ቢደረግም በባቫሪያን በፍጥነት ለመልመድ ከብዶት የሚጠበቅበትን ነገር ሜዳ ላይ ማሳየት አልቻለም፡፡

ቪዳል፣አልካንትራ እና አሎንሶ በነበሩበት የአማካይ ክፍል የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ካርሎ አንቼሎቲ በወጣቱ አዲሱ ተጫዋቻቸው ብቃት ባለመደሰታቸው እድሉን ነፍገውት በተደጋጋሚ መቀመጫ እንዲያሞቅ አደረጉት፡፡በአመቱ መጨረሻም ለባየርሙኒክ መሰለፍ የቻለው በቁጥር በዘጠኝ ጨዋታዎች ብቻ ነበር፡፡

 

ተጨዋቹ በቋሚ ቡድኑ ውስጥ ሰብሮ ለመግባት እንደሚከብደው የተረዳው ሙኒክ ሳንቼዝን በውስት ውል ሰጥቶ በቂ የመጫወት ልምድ እንዲያገኝ ወደ ስዋንሲ ላከው፡፡ብዙ የእግርኳስ ወዳጆች ይህን ዝውውር ሲሰሙ ደንግጠዋል፡፡በአንድ አመት ልዩነት ውስጥ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ፍላጎት ቀዝቅዞ የዌልሱ ስዋንሲ በውስት ውል ማስፈረም ቻለ፡፡በርግጥ ዝውውሩ እንዲፈጸም ትልቅ ሚና የተጫወቱት በሙኒክ ረዳት አሰልጣች ሆነው ከሳንቼዝ ጋር አብረው መስራት የቻሉት የአሁኑ የስዋንሲ አሰልጣኝ ፖል ክሌመንት ናቸው፡፡

1

ሳንቼዝ ጉልበት ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ በሚበዛው እና ፈጣን ውሳኔን በሚጠይቀው በእንግሊዝ ፕሪምርሊግም የራስ መተማመኑን ፈጽሞ ለመመለስ ተቸግሯል፡፡ባለፈው ሳምንት ቦርንማውዝን ገጥመው 0-0 በተለያየዩበት ጨዋታ የቢቲ ስፖርት ተንታኙ ሮቢ ሳቬጅ ጠንካራ ትችት አቅርቦበታል፡፡ “ከባርሙኒክ ጋር በቻምፒየንስ ሊጉ ተመልክቼዋለው፡፡ ከዛም ወደ ስዋንሲ መጣ፡፡ሲመጣ ይህ ልጅ ምንድ ነው ያለው? ብለህ ትጠይቃለህ::እየቀለድኩኝ አይደለም እያሳየ ያለው አቋም አሳዛኝ ነው፡፡”ሲል ተናግሯል፡፡

ትናንት ምሽትም በስታንፎርድ ብሪጅ ቼልሲን በገጠሙበት ጨዋታም ያሳየው የወረደ ብቃት ሌላ ማሳያ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡

2.jpg

ኳሶችን በትክክል ማቀበል የተሳነው ሬናቶ ሳንቼዝ 36 ኛው ደቂቃ አካባቢ ኳስ በእግሩ ቁጥጥር ስር የነበረች ሲሆን ኳሱን ለሌላኛው የቡድን ጓደኛው እንዳቀበለ አድርጎ ይመታዋል፡፡የኳሱ አቅጣጫ ወደ ቡድን ጓደኛው ሳይሆን በመስመር በኩል ወዳለው የማስታወቂያ ቦርድ ነበር፡፡በአካባቢውም ምንም አይነት የስዋንሲ ተጫዋች በቦታው አልነበረም፡፡ይልቁኑ በማስታወቂያ ቦርዱ ላይ እንደሚታየው(ምስሉን ይመልከቱ) በቀይ መደብ ላይ ያለው የካራባኦ የሀይል ሰጪ የመጠጥ ማስታወቂያ የበሬ ምስል የስዋንሲ ተጫዋች መስሎት አቀብሎታል፡፡ተጫዋቹ የተሳሳተው ደግሞ በእለቱ ስዋንሲ ለብሶት ከነበረው ቀይ ቀለም ያለው ማሊያ ከማስታወቂያው የቀይ ቀለም ጋር ተመሳሳይነት ያለው ስለነበር ነው፡፡

633088.png

“በአስደንጋጩ አቀባበል” የደነገጡት የቡድኑ አሰልጣኝ ‹ፖል ክሌመንት በድንጋጤ እራሳቸውን ይዘው በሀፍረት አንገታቸውን ደፍተዋል፡፡ተጫዋቹም በእረፍት ቀይረው አስወጥተውታል፡፡ከጨዋታው በኋላ ስለ አጋጣሚው ሲናገሩ

“በመጀመሪያም በጣም ከባድ ነገሮችን ሲያደርግ የተመለከትኳቸው ጨዋታዎች ነበሩ፡፡ነገርግን ዛሬም የተወሰኑ ኳሶች የለ አግባብ ሲያቀበል ተመልክታችሁታል፡፡የራስ መተማመኑ በጣም ወርዷል፡፡ይህ እንዲሆን እሱም አይፈልግም፡፡ከሰኞ እስከ አርብ ልምምዱን ይሰራል ስለዚህ እንዲህ አይነት ነገሮች ሊከሰትበት አይገባም፡፡”

ተጫዋቹን እረፍት ላይ ለምን እንደቀየሩት ሲናገሩ “ምንም አይነት ጉዳት አላጋጠመውም፡፡ ነገርግን በመጀመሪያ ግማሽ ደካማ እንቅስቃሴ አድረጓል፡፡ለሱ እኔ ተሰምቶኛል፡፡የራስ መተማመኑን እና አቋሙን ለማስተካከል ተቸግሯል፡፡እኔ ድጋፍ አደርግለታለው፡፤የቡድን ጓደኞቹም እንዲሁ ከሱ ጋር ናቸው፡፡”በማለት ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ጨምረው አሳውቀዋል፡፡

ሳንቼዝ በምሽቱ ጨዋታ ያስመዘገበው ቁጥራዊ ማስረጃዎች

የነካው የኳስ ብዛት – 31

በየተሳካ ሁኔታ ያቀበለው – 23

በየተሳካ ሁኔታ ያቀበለው – 66%

የተሳሳቱ ቅብብሎሽ – 9

ወደ ጎል የሞከረው – 0

አሁን ብዙ የእግርኳስ ወዳጆች ምላሽ ያላገኙለት ጥያቄ ተጫዋቹ ከአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ ከሆነ በኋላ ይህን ያህል ወርዶ የተገኘበት ምክንያት ሆኗል፡፡

 

Advertisements