እውነት ሀሰት / ሳሙኤል ኢቶ በሊቢያ በዘመናዊ ባርነት ስር ያሉ ወገኖቹን ወደ ካሜሮን እንደመለሰ እየተናፈሰ ባለው አሉባልታ ዙሪያ መልስ ሰጠ

የቀድሞው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ሳሙኤል ኢቶ በሊቢያ ምስቅልቅል ውስጥ ላሉ 10,000 የሀገሩ ዜጎች የአውሮፕላን ትኬት በመግዛት ወደሀገሩ እንደመለሳቸው የሚወራው ሀሰት መሆኑን አስታውቋል።

ኢቶ በጉዳዩ ዙሪያ ቃሉን ለመስጠት የተገደደው ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ቀናት የሀገሩን ዜጎች በሊቢያ ካለው ዘመናዊ ባርነት ለማትረፍ የአውሮፕላን ትኬት እንደቆረጠላቸውና በነፍስ ወከፍም እስከ 3,000 ዶላር እንዳበረከተላቸው የሚገልፅ ዘገባ ከምስሎች ጋር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ምንጩ ካልታወቀ ቦታ ተነስቶ ከመናፈሱ ጋር በተያያዘ ነው።   

ይህ ምንጩ በሚገባ ካልታወቀው አሉባልታ ጋር በተያያዘ በማጀቢያነት ጥቅም ላይ የዋሉት ምስሎችም ለአስርት አመታት በሊቢያ ኖረው በሀገሪቱ ካለው ብጥብጥ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የሰብአዊ ቀውስ በ 2016 ሰሜን አፍሪካዊቷን ሀገር ለቀው የወጡ የቡርኪናብ ስደተኞች ምስል መሆኑ ታውቋል።

ለአመታት በነገሰበት ኒውካምፕ ከነበረው ያማረ የባርሴሎና ቆይታ በኋላ ለኢንተር ሚላን እና ቼልሲ የተጫወተው ኢቶም በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ በለቀቀው መልዕክት በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ዘገባ እና ተያያዥ ምስል ሀሰት መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ኢቶ ታዋቂ የጥቁሮች መብት ተከራካሪ የነበረውን ማልኮም ኤክስን ምስል ማጀቢያ አድርጎ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ በለቀቀው ፅሁፍ ከሊቢያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ እሱ የበጎ ተግባር ለሀገሩ ዜጎች እንደፈፀመ በማህበራዊ ሚዲያ እየተላለፈ ያለው አሉባልታ ሀሰት መሆኑን አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ለቱርኩ አንታልያዝፑር እየተጫወተ የሚገኘው ኢቶ ከዚህ ቀደም በሀገሩ ካሜሮን በተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የመሳተፍ ልምድ ያለው መሆኑ ብዙዎች መረጃውን በቶሎ እንዲያምኑና እንዲቀባበሉት ምክንያት እንደሆናቸውም ይገመታል።  

Advertisements